ወጣቶች የፈጠራ ክህሎታቸውን በማውጣት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ይገባቸዋል

በአገሪቱ  የተለያዩ አካባቢዎች  የሚገኙ  ወጣቶች በውስጣቸው የታመቀውን  የፈጠራ ክህሎት  ወደ  አዳዲስ  ሥራ  በመቀየር ኢኮኖሚያዊ  ተጠቃሚነታቸውን  ከማረጋጋጥ  ባለፈ ለአገሪቱ አጠቃላይ  ዕድገት  የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባቸው ተመለከተ ።

በዛሬው ዕለት 4ኛው አገር አቀፍ የወጣቶች ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ  ሳይንስና ቴክኖሎጂ  ዩኒቨርስቲ በተካሄደበት ወቅት  በተዘጋጀው መድረክ  አራት  የተሻለ የሥራ  ፈጠራ  ተሞክሮና ልምድ ያላቸው ወጣቶች ለኮንፈረንሱ ወጣት ተሳታፊዎች ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ተደርጓል ።

በመድረኩ  የሥራ ፈጠራ ልምድና ክህሎታቸውን ያካፈሉት ወጣቶች  እንደገለጹት  በአገሪቱ  የሚገኙ  ወጣቶች  በተለያዩ  የሥራ  ዘርፎች  ያላቸውን እምቅ የፈጠራ ክህሎትና ችሎታ በማውጣት  ከተጠቃሚነታቸው  ባሻገር ለአጠቃላይ  የአገር ምጣኔ ሃብት  ዕድገት  አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ ብለዋል ።

በዲዛይን ዘርፍ  የራሱን ሥራ ፈጥሮ እየተንቀሳቀስ የሚገኘው  አብርሃም ተክሌ ለዋኢማ እንደተናገረው ከትንሽ ነገር ተነስቶ በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ባህላዊ ልብሶችን በመሥራት   ምርቶቹን  ወደ ውጭ  በመላክ ገቢው  ማሳደግ ችሏል ።

ሌላዋ ወጣት ምስጋና ገብረ እግዚአብሔር ከትንሽ ገንዘብ  በመነሳት  ጫማ ማምረት  መጀመሯን  ተናግራ   በአሁ ወቅት  ከአገር ውስጥ  ባለፈ ምርቶቿን  ወደ ውጭ  በመላክ  የተሻለ ገቢ እያገኘች መሆኑን  ገልጻለች ።    ለወደፊቱ   የትልቅ የጫማ  ፋብሪካ  ባለቤት  የመሆን ራዕይ እንዳላት  የጠቆመችው ምስጋና ፋብሪካውን እውን በማድረግ  እራሷን ፣ ዜጎችንና አገሯን ለመጥቀም እንደምትሠራ  ተናግራለች ።

በህክምና  ሙያ  የተመረቀው ዶክተር  አሸናፊ አንዳርጌ በበኩሉ  ከልጅነት ጀምሮ  ከመቀጠር ይልቅ  በግል ሥራ  የመሥራት  ፍላጎቱ  ከፍተኛ እንደነበር እታውሶ    በ3ሺ 500 ብር የጀመረው  የኮንስትራክሽን ሥራ  አሁን  በሚሊዮኖች ብር የሚቆጠር ሃብት  እንዲያካብት እንዳስቻለው አስረድቷል ።

በሚኖርበት የራያ አካባቢ ቋንቋ  በማስተማር የግል ሥራውን የጀመረው ወጣት አሸናፊ መረሳ እንዳለው   በአካባቢው  ያለው ችግር  በማጥናት  የቋንቋ  ማስተማር ሥራውን  መጀመረን  ጠቅሶ አበሀኑ ወቅት  የአፀደ ህጻናትና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት  ቤት ባለቤት መሆኑን ይናገራል ።

በብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የሆኑት ዶክተር አብርሃ ተከስተ በበኩላቸው በመላ አገሪቱ  በአዳዲስ የሥራ ፈጠራ በመሠማራት ህይወታቸውን ለመቀየር የሚጥሩ ወጣቶች ቁጥራቸው  ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ተናግረው  ምርጥ ተሞክሮ ያላቸው  ወጣቶች  ለተቀሩት እንዲካፍሉና  ወጣቱ ለሥራ ፈጠራ  እንዲያነሳሰሱ ለማድረግ ቀጣይ መድረኮች እየተመቻቹ መሆኑን  አብራርተዋል ።