በክልሉ ሁሉም ንግድ ቤቶች ሥራ መጀመራቸው ተመለከተ

በአማራ ክልል በተወሰኑ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ተዘግተው የነበሩ የንግድ ማዕከላት ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልሉ የሚገኙ ሁሉም የንግድ ማዕከላት ሙሉ በሙሉ ወደ ቀደመ ተግባራቸው መመለሳቸውን የቢሮው ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ለዋልታ ገልፀዋል፡፡

በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩት የንግድ ማዕከላት በተለመደው አግባብ ሥራ መጀመራቸውን የጠቆሙት ኃላፊው የንግድ ዘርፉ በሠላማዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እያለፈ ነው ብለዋል፡፡

በዘመን መለወጫና በኢድ አል አድሃ(አረፋ) በዓላት ዋዜማም ተቋማቱ በራቸውን ከፍተው የተለመደውን የንግድ ሥራ ሲያከናውኑና አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበር ኃላፊው ገልፀዋል፡፡  

በነሐሴ ወር 2008 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ የተካሄደውን ሰልፍ ተከትሎ በተፈጠረው ግጭት የተወሰኑ ንግድ ቤቶች መዘጋታቸውን አቶ ተስፋዬ አስታውሰዋል፡፡ ሆኖም ግጭቱ ከተረጋጋ በኋላ የንግድ ማዕከላቱ ሥራ ጀምረዋል ብለዋል፡፡

ግጭቱን ተከትሎ አንዳንዶች ምርቶችን ለመከዘንና ዋጋ ለመጨመር ያደረጉት ሙከራም ሸቀጦችና የተለያዩ ምርቶችን በሚያቀርቡ ህብረት ሥራ ማህበራት ተሳትፎ አማካኝነት ሊከሽፍ መቻሉን አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡

በተለይም በነሐሴ ወር 2008 ዓ.ም መጨረሻ የጤፍ ምርት ዋጋን ለማናር የተደረገው ጥረት ማህበራቱ የጤፍ ምርትን በሚዛናዊ ዋጋ በብዛት በማቅረባቸው ሊሳካ አለመቻሉን አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል፡፡

በአንዳንድ አካላት ‹‹በክልሉ የሚገኙ ንግድ ቤቶች ሥራ አቁመዋል›› በሚል የሚናፈሰው ወሬ ከእውነታው የራቀና መሰረተ ቢስ መሆኑን ነው ኃላፊው የገለፁት፡፡ አሁንም ሥራ የጀመሩ ንግድ ቤቶች እንደሚዘጉ የሚነዛው ወሬ ውሸት ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይም ምርቶችን ከህግ አግባብ ውጭ የመከዘንና ዋጋ ለማናር የሚደረግ ሙከራ እንዳይኖር ቢሮው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንደሚሰራ ነው ያስረዱት፡፡