አጄንሲው የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመሥጠት ቅድመ ዝግጅቶችን በሙሉ አጠናቋል

የአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ በ11ኛው ዙር የጋራ  መኖሪያ ቤት  እድለኞች  ለሆኑ ዜጎች የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመሥጠት ቅድመ ዝግጅቶችን ሙሉ ለሙሉ ማጠናቀቁን   አስታወቀ ።

የኤጀንሲው ሥራ አስኪያጅ አቶ ሽመልስ ታምራት በዛሬው  ዕለት ለጋዜጠኞች በሠጡት መግለጫ  እንደገለጹት ሐምሌ 30 /2008 ዓም የጋራ መኖሪያ ቤቶች  የወጣላቸው ዜጎች   በቦሌና በአቃቂ ክፍለ ከተሞች በተዘጋጁላቸው የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለማስተናገድ  የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች  ተጠናቀዋል ።

ከዚህ ቀደም በነበሩት የ10 ዙር የጋራ መኖሪያ ቤቶች የማስተላላፍ ሂደት የቤት  ተጠቃሚዎች  በርካታ እንግልትና ውጣውረዶች እንደሚያጋጥማቸው ያስታወሱት አቶ ሽመልስ በሚጀምረው የአንድ ማዕከል አገልግሎት አንድ የጋራ  መኖሪያ ቤት  ተጠቃሚ ቤቱን ለመረከብ አንድ  ዓመት ሲፈጅበት  የነበረው የማስተላላፍ ሂደት  በአንድ ቀን ለማጠናቀቅ የሚያስችል ነው ብለዋል ።

የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ የጋራ መኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም ቁልፍ ለመረከብ ፣ የይዞታ ካርታ ለመውሰድ ፣ ከባንክ ጋር የተያያዙ ውሎችን ለመፈጸም  የሚፈጀውን ጊዜ  በመቀነስ ሶስቱንም አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል ፣ ዘመናዊና  በተቀላጠፈ መልኩ  አገልግሎትን  ለመሥጠት የሚያስችል መሆኑን  አቶ ሽመልስ አመልክተዋል ።

የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ  ከመጪው ሰኞ መስከረም 9  እስከ  ህዳር 19  ድረስ  በቦሌና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማዎች  በተዘጋጁት  ማዕከላት አገልግሎቱ የሚሠጥ መሆኑን ያብራሩት  አቶ ሽመልስ ማንኛውም የቤት እድለኛ  የሚጠበቁበትን  ቅድመ ሁኔታዎችን በሟሟላት በአጭር ጊዜ ውስጥ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችል ገልጸዋል።

አጀንሲው በ11ኛው የጋራ መኖሪያ ቤት  ተጠቃሚዎችን  የሚያስተናግደው የብሎክ ቁጥሮችን መሠረት አድርጎ በሚያወጣቸው የጊዜ ሰሌዳና መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሽመልስ  ማንኛውም  ተገልጋይ  የሚስተናገድበትን የጊዜ ሰሌዳ በየክፍለ ከተማዎች የሚለጠፍ መሆኑንና በአዲስአበባ አስተዳደር ድረገጽ ላይ መመልከት እንደሚችል አስረድተዋል ።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮሚኒኬሽን ክፍል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ  በበኩላቸው ባንኩ የጋራ መኖሪያ ባለዕድለኞች ሳይንገላቱ የብድር ውል አገልግሎት  ለመሥጠት  በቦሌና አቃቂ ክፍለ ከተማዎች  ማዕከላት በመክፈቱ ጠቅሰው ለወደፊቱም  ማዕከላቱን  በተቀሩት ክፍለ ከተማዎች ለመክፈት ማቀዱን ተናግረዋል ።