ለክልሉ ወጣቶች በውጭና አገር ውስጥ የገበያ ትስስር እየተፈጠረ ነው

በአማራ ክልል በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ በመደራጀት ለሚንቀሳቀሱ ወጣቶች በውጭና አገር ውስጥ የገበያ ትስስር እየተፈጠረላቸው መሆኑ ተመለከተ፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለ61 ሺ ማህበራት የገበያ ትስስር ለመፍጠር ታቅዶ ለ45ሺ ኢንተርፕራይዞች የገበያ ትስስር መፈጠሩን የአማራ ክልል የቴክኒክ፣ሙያና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ምትል ኃላፊ አቶ ካሣ ዓለሙ ለዋልታ ተናግረዋል፡፡

ከተፈጠረው የገበያ ትስስርም 70 ያህል ኢንተርፕራይዞች የውጭ ገበያ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን አቶ ካሳ ገልፀዋል፡፡ የገበያ ትስስር ተጠቃሚ የሆኑት ኢንተርፕራይዞች ከ143ሺ በላይ አንቀሳቃሾችን ማቀፋቸውንም አስረድተዋል፡፡

በአገር ውስጥ ገበያ ከሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር፤ በውጭ ገበያ ደግሞ ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር በላይ የገበያ ትስስር ለመፍጠር መቻሉን ነው ምክትል ኃላፊው የተናገሩት፡፡

የገበያ ትስስሩ ዕድገት ተኮር በሆኑት ማፋክቸሪንግ፣ኮንስትራክሽንና ከተማ ግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ ማህበራት ትኩረት የሰጠ ነው ብለዋል-አቶ ካሣ፡፡

ለውጭ ገበያ ከቀረቡት ምርቶች ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ ሲሆን ዕሴት የተጨመረበት የዓሣ ምርትና የባልትና ውጤቶችም መካተታቸውን አስረድተዋል፡፡

አሜሪካ፣ አረብ አገራት፣ ሱዳንና ጅቡቲም የውጭ ገበያ ትስስሩ የተፈጠረባቸው አገራ መሆናቸውን ምክትል ኃላፋ ፀቁሟል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ለ83ሺ ማህበራት የሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ ገበያ ትስስር ለመፍጠር ታቅዷል፡፡ በውጭ ገበያም ለ110 ማህበራት ሶስት ሚሊዮን ዶላር የገበያ ትስስር ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ነው የተመለከተው፡፡

በአማራ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ለ920ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን ከክልሉ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡