ኢትዮጵያ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ የተሻለ ደረጃ ለመሸጋገር የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ ቻይና የበኩሏን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል በአፍሪካ ሕብረት የቻይና አምባሳደር ኲዋንግ ዌሊን ገለጹ፡፡
አምባሳደሩ የቻይና 67ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በትላንትናው ዕለት በተከበረበት ወቅት ባሰሙት ንግግር ኢትዮጵያና ቻይና ለብዙ ዓመታት የዘለቀ ወዳጅነታቸውንና ትብብራቸውን በማሳደግ ለጋራ ተጠቃሚነትና የበለጠ ዕድገት ለማስመዝገብ ይሰራሉ፡፡
የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር መስመርና የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ግንባታዎች፣ ሁለቱ አገሮች በትብብር እያከናወኗቸው ካሉት ጉልህ ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ እንደሆኑ አምባሳደሩ አክለው ገልጸዋል፡፡
የቻይና መንግስት የአፍሪካን የ2063 የልማት አጀንዳ እውን ለማድረግ አህጉሪቷ የምታደርገውን ጥረት ለማሳካት የምትሠጠውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥና ባሳለፍነው ህዳር በጆሀንስበርግ በተደረገው ስብሰባ ላይ ቻይና የ60 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ለአፍሪካ ድጋፍ እንዳደረገች አምባሳደሩ አስታውሰዋል፡፡
እንደ አምባሳደር ኲዋንግ ንግግር ቻይና በመንገድ፣ ባቡርና ኢንደስትሪ ልማት ግንባታዎች እንዲሁም አፍሪካን በመሠረተ ልማት ኔትዎርክ ለማስተሳሰር የምታድርገውን ድጋፍ ይበልጥ አጠናክራ ትቀጥላለች፡፡
የኢትዮጵያና ቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1970 እንደተጀመረ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡