ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የትልቅ ኢኮኖሚ ባለቤትነትን ዘንድሮ ከኬንያ ትረከባለች – አይ ኤም ኤፍ

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የትልቅ ኢኮኖሚ ባለቤትነትን በቅርቡ ከኬንያ እንደምትረከብ አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ገለጸ።

አይ ኤም ኤፍ የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በተመለከተበት ሪፖርቱ፥ ኢትዮጵያ በተያዘው የፈረንጆቹ አመት የቀጠናውን የኢኮኖሚ መሪነት ከኬንያ እንደምትረከብ ይገልጻል።

ኢትዮጵያ ለተከታታይ 10 አመታት ባለ ሁለት አሃዝ እድገት ማስመዝገቧን የጠቀሰው ሪፖርቱ፥ እየተመዘገበ ያለው እድገት የህዝብ መገልገያ መሰረት ልማቶችን ያማከለ መሆኑንም ገልጿል።

ጠቅላላ የሃገር ውስጥ ምርት እድገቱም ባለፈው አመት ከነበረበት 61 ነጥብ 62 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በዚህ አመት ወደ 69 ነጥብ 21 ቢሊየን ዶላር እንደሚያድግም ነው የተቋሙ ሪፖርት የጠቀሰው።

ይህም ሊጠናቀቅ ሶስት ወራት በቀሩት የፈረንጆቹ አመት ከነበረበት 63 ነጥብ 39 ቢሊየን ዶላር ወደ 69 ነጥብ 17 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያድግ ከሚጠበቀው የኬንያ ጠቅላላ የሃገር ውስጥ ምርት እድገት አንጻር ከፍ ያለ መሆኑም በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

የኬንያ ጠቅላላ የሃገር ውስጥ ምርት እድገት በፈረንጆቹ 2000 ላይ ከኢትዮጵያ ከ71 በመቶ በላይ ብልጫ እንደነበረው ያወሳው ሪፖርቱ፥ ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት ባስመዘገብችው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ልዩነቱ መጥበቡንም ነው የገለጸው።

ይህ የኢኮኖሚ መሪነት ሃገሪቱን የኢንቨስትመንት መዳረሻ በማድረግ የተያዘውን እድገት ለማስቀጠል እንደሚረዳም ነው የተቋሙ ሪፖርት የሚያመለክተው።

እንደ ሪፖርቱ ገለጻ፥ ኢንቨስትመንት ከጠቅላላው የሃገር ውስጥ ምርት እድገት አንጻር ያለው ድርሻ በፈረንጆቹ 2000 ከነበረበት 20 ነጥብ 2 በመቶ በዚህ አመት ወደ 39 ነጥብ 2 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ከጎረቤት ኬንያ (በተያዘው አመት ከነበረበት 21 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 22 ነጥብ 5 በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል) የተሻለ እድገት እንዳለው ነው ሪፖርቱ የሚገልጸው።

ተቋሙ በሪፖርቱ እንደገለጸው፥ ኢኮኖሚያዊ እድገቱ የዜጎችን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ መሰረተ ልማቶች የተደገፈ እና ቀጣይነት ያለው ነው።

ከዚህ ባለፈም ሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገቱን ለማስቀጠል የሚረዱ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ መሆኗም በሪፖርቱ ጠቅሷል።

ለዚህም ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር ፕሮጀክትን በአብነት ያነሳል።

ተቋሙ በሪፖርቱ እነዚህ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ የሃገሪቱን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው ብሏል።

ሃገሪቱ የገነባችው ጠንካራ ኢኮኖሚም በቅርቡ የተከሰተውን አስከፊ ድርቅ በራስ አቅም መቋቋም እንዳስቻላትም ነው የተቋሙ ሪፖርት የሚያነሳው።(ኤፍቢሲ)