የምክር ቤቱ አባላት ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉ ገለጹ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ከዳር ለማድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት አባላት ተናገሩ።

አባላቱ የግድቡ ግንባታ ሲጀመር የገቡትን ቃል በማደስ ተጠናቆ ስራ እስኪጀምር ድረስ በገንዘብና በእውቀት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የተናገሩት።

ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ እንዳለው "ግድቡን በተመለከተ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ካላቸው የኔነት ስሜት በላይ አንድ የሆነ ጠንካራ አቋም ሊኖረን ይገባል"።

"ለግድቡ ሊሰማን የሚገባው ኃላፊነት ከገንዘብም በላይ ነው" ያለው አትሌት ኃይሌ ለፕሮጀክቱ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል ገልጿል።

በገንዘብ ከሚደረገው ድጋፍ በተጨማሪ ስለግድቡ ትክክለኛ መረጃ ለትውልድና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማስተላለፍ ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ነው የገለጸው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ፅህፈት ቤት ተወካይ አባ ሠረቀብርሃን ወልደአማኑኤል የግብፅ ህዝብና መንግስት በአገራቸውና በአባይ ጉዳይ ያላቸው አንድነትና አቋም የእኛም የህልውና ጉዳይ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ቤተ ክርስቲያኗ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባትና ያሏትን ተከታዮች በማንቀሳቀስ ቀደም ሲል ለግድቡ ስታደርገው የነበረውን ድጋፍ  እንደምትቀጥልም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አልሃጂ ሙሐመድ አሚን ጀማል በበኩላቸው ህዝበ ሙስሊሙ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

በዚህ መልክ ከህዝበ ሙስሊሙና ከእምነት ተቋሙ የሚደረገው ድጋፍ ግድቡ እስከሚጠናቀቅ እንደማይቋረጥም ነው የገለጹት።

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከሕዝብ 8 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የግንባታው ሂደት 54 በመቶ ደርሷል።(ኢዜአ)