ልማት ባንክ ለሊዝ ፋይናንስ ማስፈጸሚያ ከ6ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ መድቧል

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በዘንድሮ የበጀት ዓመት ለሊዝ ፋይናንስ ሥርዓት ማስፈጸሚያ  ከ 6ነጥብ 9  ቢሊዮን  ብር በላይ መመደቡን አስታወቀ ።

የባንኩ  ኮርፖሬት ኮሚኒኬሽንና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር ዶክተር በኃይሉ ካሳዬ ለዋልታ እንደገለጹት ልማት ባንክ  በአብዛኛው ወጣቶች በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሠማሩ በማድረግ በአገሪቱ የኢኮኖሚ፣ማህበራዊና ቴክኖሎጂ ሽግግርን እንዲጠናከር ለማስቻል እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል ።

በአገሪቱ  የተደራጁ ወጣቶች  በአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ባንኩ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት  የሊዝ ፋይናንሲንግ ድጋፍ  እንደሚደረግላቸው  የጠቆሙት ዶክተር በኃይሉ  በመላ አገሪቱ  የሊዝ ፋይናንስ ሥርዓቱን ለማስፈጸም ባንኩ 75 አዳዲስ  ቅርንጫፎችን  መክፈቱን ተናግረዋል ።

ባለፉት ሦስት ወራት በርካታ የብድር ጥያቄዎች  መቅረባቸውን ያስረዱት  ዶክተር  በኃይሉ  በሦስት ወራት   ውስጥ   550  ሚሊዮን ብር  የሚያወጡ  የካፒታል  እቃዎች  88  ለሚደርሱ ኢንተርፕራይዞች በሊዝ ፋይናንስ ሥርዓት አማካኝነት ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል ።

የልማት  ባንክ  በተለይ በእርሻ ፣ በግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያ፣ የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶችና በማዕድንና በኮንስትራክሽን ምርቶች  ለተሠማሩና ኢንተርፕራይዞች  በሊዝ ፋይናንሲንግ ሥርዓቱ አማካኘነት የካፒታል እቃዎችን በመግዛት ድጋፍ እያደረገ  እንደሚገኝ  ዶክተር  በኃይሉ አመልክተዋል ።

የፌደራልአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ልማት ለወጣቶች ሥልጠና በመሥጠት፣ እንዲደራጁ   በማድረግ   ወደ ኢትዮጵያ  ልማት ባንክ እየላከ መሆኑንና  ባንኩ በሊዝ  ፋይናንስ  ሥርዓቱ  የማምረቻ  ካፒታል  እቃዎች በማቅረብ  ለወጣቶች  ሰፊ  የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ጥረት  እየተደረገ  መሆኑንም ዶክተር በኃይሉ  አያይዘው ገልጸዋል ።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን በሊዝ  ፋይናንሲንግ ሥርዓት የካፒታል እቃዎችን  ለ 3ሺ አምራች እንተርፕራይዞች  ለማቅረብ እንዲያስችለው በአጠቃላይ  42  ቢሊዮን ብር  መመደቡን  ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል  ዘግቧል  ።