ባለሥልጣኑ የተሻሻለውን የተገልጋዮች ቻርተር ተግባራዊ ሊያደርግ ነው

የገቢዎችና  ጉምሩክ  ባለሥልጣን  ቀደም  ሲል የነበረውን  የተገልጋዮች  ቻርተር ላይ  ማሻሻያ በማድረግ  ሥራ ላይ  ሊያውል መሆኑን አስታወቀ ።

በባለሥልጣኑ የደንበኞች አገልግሎት ዳይሮክቶሪየት ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ሽፈራው ለዋልታ እንደገለጹት ባለሥልጣኑ ባለፈው ዓመት ተግባራዊ ያደረገውን የደንበኞች ቻርተር ላይ  ከተገልጋዩ ህብረተሰብና ከባለድርሻዎች ግብዓት በመሰብሰብ በቻርተሩ ላይ ማሻሻያ አድርጓል ።

አዲሱ የተገልጋይ ቻርተር በአገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብና የጉምሩክ የአሠራር ደረጃዎች እንዲሁም የደንበኞች ቅሬታዎች አሠጣጥ ላይ  ማሻሻያዎች የተደረጉ መሆኑን  አቶ ዮሴፍ  ጠቁመው አዲሱ የተገልጋዮች ቻርተር ከህዳር ወር ጀምሮ በሁሉም የባለሥልጣኑ ቅርንጫፎች ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል ።

ከሚቀጥለው  ወር ጀምሮ  ሥራ ላይ የሚውለውን  የተገልጋዮች ቻርተርን ሙሉ  ለሙሉ ተግባራዊ  ለማድረግ ከግንዛቤ ማስጨበጫ ጀምሮ ለባለሥልጣኑ ሠራተኞችም ሥልጠና   መሠጠቱን  አቶ ዮሴፍ ተናግረዋል ።

በተለይም አዲሱ የተገልጋይ ቻርተር ከአዲሱ የግብር አዋጅ ጋር የተጣጣመ እንዲሆንና የተሻለ አገልግሎት እንዲኖር ለማስቻል ከህዝብ ክንፉ ጋር ሰፋፊ ውይይቶችም መካሄዳቸውን አቶ ዮሴፍ አያይዘው ገልጸዋል ።

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ለደንበኞቹ የሚሠጠውን የአገልግሎት ደረጃ ለማሻሻል የአንድ መስኮት አገልግሎት ከመጀመሩም ባሻገር ከጥቅምት 15 ፤2008 ዓም ጀምሮ  የተገልጋይ ቻርተርን ተግባራዊ አድርጓል ።