ኢንስቲትዩቱ ከቆዳ አልባሳትና ዕቃዎች ከ26 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ አገኘ

የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከቆዳ አልባሳትና ዕቃዎች ወደ ውጭ አገሮች በመላክ ከ26 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ገለጸ ፡፡

የኢንስቲትዩቱ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ስርጀቦ ለዋልታ እንደገለጹት በሩብ  በጀት ዓመት ከጫማ፣ የቆዳ አልባሳትና ዕቃዎች ወደ ተለያዩ የውጭ አገሮች 49ሚሊየን 488 ሺ 980 ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 26ሚለየን 87ሺ 150 ዶላር ገቢ ለማግኘት ተችሏል ፡፡

ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት አፈፃፀም ጋር ሲነጻጸር ወደ ውጭ ከተላኩት የቆዳ ጓንትና ያለቀለት ቆዳምርቶች ላይ መቀነስ ያሳየ ሲሆን የጫማ ፣የቆዳ አልባሳትና ዕቃዎች በመጠኑ መጨመሩን አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም ይህን ክፍተት በመሙላት ኢንስቲትዩቱ  በዘላቂነት የቆዳ ኢንዱሰትሪው በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግና የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት በሀገር ውስጥ እና በውጭ አገር ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትስስር መፈጠሩ አስረድተዋል፡፡

በዚህም በዘርፉ  እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ የሰለጠኑ  በርካታ መሃንዲሶችና ባለሙያዎችን የማፍራት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ነው ያመለከቱት ፡፡

በመላው ሀገሪቱ ከ32 በላይ በሆኑ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች ጋር በመተባበርም በቆዳ ውጤቶች ቴክኖሎጂ እስከ ደረጃ አራት በርካታ ወጣቶች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል ፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ከ10 በላይ ችግር ፈች ምርምሮች እየተካሄዱ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡

ይህም የወቅቱን የዓለምን ፋሽን አቅጣጫ በመከተል በዘርፉ በርካታ ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን  በብዛት እያመረቱ ለገበያ እንዲያቀርቡ መደረጉ አመልክቷል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በቅርቡ የዓለም አቀፍ የጥራት ማኔጅመንት ሰርተፊኬት ባለቤት መሆኑን ነው የጠቆሙት ፡፡

በዚሁም ከሀገራችን ወደ ውጭ የሚወጡ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች እሴት የተጨመረባቸውና  በኢንስቲትዩቱ ላቦራቶሪ ተፈትሸው የጥራት ማረጋገጫ እንደሚሰጣቸው ሃላፊው ገልጸዋል ፡፡

በዚሁም በአነስተኛና መካከለኛ የጫማና የቆዳ ውጤቶች የተሰማሩ ድርጅቶች ከትላልቅ የጫማና የቆዳ ውጤቶች ጋር እንዲተሳሰሩ በማድረግም ለውጭ ገበያ ምርቶችን እያቀረቡ ይገኛሉ ነው ያሉት ፡፡