ሞኤንኮ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሚያገለግሉ ሶስት መኪኖችን አበረከተ

የኢትዮጵያ ሞተርና ኢንጂነሪንግ ኩባንያ አክሲዮን ማሕበር (ሞኤንኮ) ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባሰቢያ የሚሆኑ ሶስት ፒክአፕ መኪኖችን በስጦታ መልክ አበረከተ፡፡

በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ ዛሬ የተገኙት የገንዘብና ኤኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትር ዶክትር አብርሃም ተከስተ ግምታቸው 8ነጥብ25 ሚሊየን ብር ዋጋ ያላቸው ዘመናዊ ፒክአፕ መኪኖቹን ቁልፍ ከሞኤንኮ ሥራ አስፈፃሚ ተረክበዋል ፡፡

በዚሁ ወቅት ዶክተር አብረሃም እንደገለጹት ፤ለሞኤንኮ ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ በቀጣይም ኩባንያው ድጋፉን አጠናክሮ እደሚቀጥል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሌሎች እንደ ሞኤንኮ ሁሉ የግል ኩባንያዎችም ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

መኪኖቹ ግድቡን ለማጠናቀቅ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማስገኘት የገቢ ማሳባሰቢያ አማራጮች በመሆን ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው ነው የገለጹት ፡፡

የሞኤንኮ ሥራ አስፈፃሚ  ክሪስ ዲ ሙይንክ በበኩላቸው ፤ ሞኤንኮ በኢትዮጵያ የትርንስፖርት አገልግሎት ላይ ያለውን አሰተዋጽኦ ከማገዝ ባሻገር የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

ኩባንያው ቀደም ሲል 900 ሺህ ብር የሚያወጣ ቶዮታ ያሪስ በስጦታ መልኩ እንዳበረከተና የ23 ሚሊየን ብር ቦንድ ግዢ እንዳከናወነም ሥራ አስፈጻሚው አንስተዋል፡፡

ዘንድሮ ለግድቡ ግንባታ ገቢ ማሰባሰቢያ ሁለት ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ እተየሰራ እንደሆነ ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሕዝብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ 11 ሺ የሚሆኑ ወጣቶችና 350 የዘርፉ ባለሙያዎች ቀንና ማታ በግንባታው ላይ እየተሳተፉ እነደሆነ ይታወቃል፡፡

የመሰረት ድንጋዩ መጋቢት 24፣ 2003 የተቀመጠው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አሁን ላይ 54 በመቶ እንደደረሰ መገለጹን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡