6ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ኮንፈረንስ ዝግጅት ተጠናቋል

በመጪው ህዳር 7 እና 8 የሚካሄደውን 6ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ ፣የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ኮንፈረንስን  በስኬት ለማካሄድ  ዝግጅቶች በሙሉ መጠናቀቃቸው  ተገለጸ ።

በንግድ ሚኒስቴር የውጭ  ንግድ ማስፋፊያ ዳይሮክቶሪየት ጀነራል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ አሰፋ ሙሉጌታ በዛሬው ዕለት በሠጡት መግለጫ እንደገለጹት በመጪው ህዳር 7 እና 8 በአዲስ አበባ ኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል ለሚካሄደው 6ኛው ዓለም ዓቀፍ የጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማቅመም ኮንፈረንስ በስኬት ለማካሄድ አስፈላጊ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል ።     

ኮንፈረንሱ ስኬታማ እንዲሆን ለማድረግ  የንግድ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ  ጥራጥሬ  ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር ተቀናጅተው  እየሠሩ ስለመሆኑ  አቶ አሰፋ  በሠጡት መግለጫ ተናግረዋል ።

ኮንፈረንሱ  “ የግብርና ምርቶች  ግብይት  ቀጣይነት ላለው  ዓለም አቀፍ ንግድ” በሚል  መሪ ቃል እንደሚካሄድ የጠቆሙት አቶ አሰፋ  በአጠቃላይ  110 የውጭ አገር እና 160 የሚደርሱ የአገር ውስጥ  ተሳታፊዎች እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ ሲሆን እስካሁን 75 የውጭ አገርና 137 የአገር ውስጥ በዘርፉ  የተሰማሩ የባለድርሻ አካላት ተሳታፊዎች ተመዝግበዋል ብለዋል ።

ኢትዮጵያ ይህን  ኮንፈረንስ ማዘጋጀቷ  በጥራጥሬ ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማቅመም ምርቶች የወጪ ንግድና የገበያ ትስስሩን ለማሳደግ እንደሚያግዝ የሚገልጹት አቶ አሰፋ   የዓለም የጥራጥሬ፣ቅባት እህሎችና ቅመማቅመም ላኪዎችንና ገዢዎችን በአንድ መድረክ በማገናኘት  ልምድ  ለመቅሰም የሚያግዝ መሆኑ ተመልክቷል ።

የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት አህሎችና ቅመማቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር ፕሬዚደንት የሆኑት አቶ ሃይሌ በርሄ በበኩላቸው እንደዚህ አይነት  ኮንፈረንስ በአገሪቱ በተከታታይ ጊዜ መካሄዳቸው በዘርፉ  የግብይት  ሁኔታውን የሚወስኑ ባለድርሻዎች የሚገኙበት በመሆኑ ለአገሪቱ  የገጽታ ግንባታ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል ።

እንደ አቶ ሃይሌ ገለጻ  ከሳምንት በኋላ በሚካሄደው  6ኛው ኮንፈረንስ ባለፈው የበጀት ዓመት  በአገሪቱ  በቅባት አህሎች፣ በጥራጥሬና ቅመማ ቅመም የተሻለ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ላስመዘገቡ እውቅና ይሠጣል ።