ኢትዮጵያ በሩብ ዓመቱ ከወጪ ንግድ 640 ነጥብ9 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቷ ተገለጸ

ባለፉት ሦስት ወራት ከወጪ ንግድ 640 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የንግድ ሚኒስቴር  አስታወቀ ።

በሚኒስቴሩ የወጪ ንግድ ማስፋፊያ ዳይሬክተር ጀነራል የሆኑት አቶ አሰፋ ሙሉጌታ ለዋልታ እንደገለጹት በዘንድሮ የበጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት 640 ነጥብ9 ሚሊዮን  ዶላር ገቢ የተገኘው የተለያዩ የግብርና፣ የማኑፋክቸሪንግና የማዕድን ምርቶች  ወደ  112  የዓለም አገራት  በመላክ ነው ።

ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር አገሪቱ ከወጪ ንግድ ያገኘቺው ገቢ በ46 ሚሊዮን  የአሜሪካ ዶላር  መቀነሱን የጠቆሙት አቶ አሰፋ በተለይም የግብርናና የማዕድናት ምርቶች ከፍ ባለ መጠን ወደ ውጭ ቢላኩም በዓለም ገበያ የግብርናና የማዕድናት ዋጋ በመውረዱ ምክንያት ለገቢው መቀነስ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ተናግረዋል ።

በሩብ ዓመቱ ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች በተነጻጻሪነት ከቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬ፣ቅመማቅመምና  የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች  ከዓምናው ተመሳሳይ ጊዜ የተሻለ ገቢ  ማስገኘታቸውን   አቶ  አሰፋ  አክለው ገልጸዋል ።

እንደ አቶ አሰፋ  ማብራሪያ  ለወደፊቱ አገሪቷ ወደ ውጭ የምትልካቸውን የተለያዩ ምርቶች  ላይ እሴት በመጨመርናየምርት  ጥራት ላይ ማሻሻያ በማድረግ ይበልጥ ከምርቶቹ የሚገኘውን ገቢ  ማሳደግ ያስፈልጋል  ።

ባለፉት ሦስት ወራት  የኢትዮጵያን ምርቶች  በመግዛት  ከፍተኛ የውጭ  ምንዛሪ  በማስገኘት  ሶማሊያ፣ ቻይና ፣ኔዘርላንድስ ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ እና ጀርመን  ከአንድ አስከ አምስት ያለውን ደረጃ  መያዛቸውን አቶ አሰፋ ተናግረዋል ።

ኢትዮጵያ  በዘንድሮ የበጀት ዓመት ከወጪ ንግድ  4ነጥብ7 ቢሊዮን  የአሜሪካ ዶላር  ለማግኘት አቅዳለች ።