ኮሚሽኑ በሁከቱ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ኢንቨስትመንቶች ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ

በሀገራችን አንዳንድ አከባቢዎች በነበረው ግጭት ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸው የኢንቨስትመንት ፕረጀክቶች መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ ፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍጹም አረጋ የ2009ዓመተ ምህረት የመጀመሪያ ሩብ በጀት ዓመት አፈጻጸምን አስመልክቶ በትናንትናው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ላይ የነበሩ 47 ፕሮጀክቶች ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው አረጋግጠዋል ፡፡

ከነዚሁም ውስጥ 44 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ መግባታቸውን ነው ያስታወቁት ፡፡

ጉዳት ከደረሰባቸው 24 የአበባና ፍራፍሬ ፕሮጀክቶች 23ቱ እና እንደዚሁም በኢንዳስትሪ ዘርፍ ከተሰማሩ 23 ፕሮጀክቶችም 21 ሥራ መጀመራቸውን አብራርተዋል፡፡

እነዚህ ኢንቨስትመንቶች  ንብረታቸው ላይ የደረሰውን ጉዳት በመንግስት ተጠንቶ እንደሚተካላቸውና ከቀረጥ ነፃን ጨምሮ የአንድ ዓመት የግብር እፎይታም እንደሚደረግላቸው አቶ ፍጹም አስታውቀዋል ፡፡

በዚሁ አጋጣሚም የተሟላ የመድህን አገልግሎት ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ነው ኮሚሽነሩ ያስገነዘቡት ፡፡

በባለ ሃብቶችና በተወሰኑ የመድህን ኩባንያዎች መካከል  ለተከሰተው የካሳ ክፍያ ችግር ከብሔራዊ ባንክ ጋር በመወያየት የመድህን ኩባንያዎች ላይ ፍተሻ እንደሚደረግም አመልክተዋል ፡፡

በሩብ በጀት ዓመቱ ከግማሽ ቢልዮን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡  

በ2009 በጀት ዓመት 124 የውጭ ባለሃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን በሀገሪቱ ለማፍሰስ  ከተስማሙት ውስጥ 71 የቻይና ባለሃብቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል ፡፡

መንግስት በተለይም ለባቡር፣ ለቴሌኮም፣ ለመንገድ እና ለኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ግንባታ የሰጠው ትኩረት ባለሃብቶች  ይበልጥ እየሳበ መምጣቱን አስረድተዋል ።

ኮሚሽነሩ በሩብ ዓመቱም ከ3 ነጥብ 5 ቢልዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ዕቅድ ያላቸውን የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ቀጣይ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንደሚገቡ ኮሚሽነሩ ማመልከታቸውን ዋልታ ኢንፈርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ፡፡

ኤዲተር በሪሁ ሽፈራው