ከሦስት ዓመት በፊት ግንባታው ተጀምሮ በሚጠበቀው ሁኔታና የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ ያልቻለው የሐዋሳ- ጩኮ የ66 ኪሎሜትር የመንገድ ግንባታ ለሌላ የሥራ ተቋራጭ መሠጠቱን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ ።
በባለሥልጣኑ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለዋልታ እንደገለጹት የትራንስ አፍሪካ ሃይዌይ መንገድ አካል የሆነው የ66 ኪሎሜትር እርዝመት ያለው የሐዋሳ-ጩኮ መንገድ 958 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በህንዱ ኤስ ኢደብሊው በተባለ ኩባንያ ግንባታው ሲከናወን ቆይቷል ።
ሆኖም ኩባንያው የመንገዱን ግንባታ ለማጠናቀቅ ሦስት ዓመት የተሠጠው ቢሆንም በተሠጠው የጊዜ ሰሌዳ 33ነጥብ 8 በመቶ ብቻ በማጠናቀቁና የግንባታው ጥራት ባለመጠበቁ ከተለያዩ ማስጠንቀቂያዎች በኋላ ባለሥልጣኑ ከኩባንያው ጋር የነበረውን ውል መሰረዙን አቶ ሳምሶን አስረድተዋል።
እንደ አቶ ሳምሶን ማብራሪያ ባለሥልጣኑ የሐዋሳ -ጩኮ መንገድ ፕሮጀክትን ለማከናወን ጥሩ አፈጻጻም ያላቸውን ሰባት የሥራ ተቋራጮች በጨረታ በማወዳደር ለሲኖ ሃይድሮ ኮርፖሬሽን ለተባለ የቻይና ኩባንያ በሁለት ዓመት ገንብቶ እንዲያስረክብ የሠጠ ሲሆን ለግንባታው በአጠቃላይ 965 ሚሊዮን 247ሺ ብር ተመድቧል ።
የሐዋሳ-ጨኮ የመንገድ ግንባታ በሦስት ኮንትራት ተከፋፍሎ ግንባታው የሚከናወነው የሐዋሳ-አገረማሪያም የ198 ኪሎሜትር መንገድ አካል ሲሆን ግንባታው ሙሉ ሙሉ ሲጠናቀቅ አዲስ አበባን ከኬንያ ሞምባሳ ወደብ ጋር በቀጥታ ያገናኛል ተብሎ ይጠበቃል ።
የሐዋሳ -ጩኮ መንገድ ፕሮጀክት ሙሉ ወጪ የሚሸፈነው በአፍሪካ ልማት ባንክና በኢትዮጵያ መንግሥት መሆኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።