የቤት ዕድለኞች የውል መፈፀሚያ ጊዜ ተራዘመ

የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ኤጄንሲ በ11ኛው ዙር የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ ደርሷቸው ለነበሩ ዕድለኞች ለ60 ቀናት አስቀምጦ የነበረውን ውል የመፈፀሚያ ጊዜ ገደብ ማራዘሙን አስታወቀ፡፡

ቀደም ሲል ለዕድለኞች ለውል መፈፀሚያ የተቀመጠው ጊዜ ገደብ ዛሬ እንደሚያበቃ የኤጄንሲው ዋና ዳይሬክተር ሽመልስ ታምራት ተናግረዋል፡፡

በገንዘብ እጥረትና በተለያዩ ምክንያቶች ውሉን መፈፀም ያልቻሉ በርካታ ዕድለኞች ተጠቃሚ ለማድረግ ሲባል ጊዜ ገደቡን ለ15 ቀናት ማራዘሙን ገልጿል፡፡

የዕድለኞች የሥም የፊደል ስህተትና የስም ለውጥ ውሉን ለመፈፀም ተጨማሪ ተግዳሮቶች እንደነበሩ አቶ ሽመልስ ተናግረዋል፡፡ እነዚህና መሰል ምክንያቶችን መሰረት በማድረግ ጊዜ ገደቡ መራዘሙን አስረድተዋል፡፡

አቶ ሽመልስ እንዳሉት ስምንት ሺ ያህል የሚሆኑ ዕድለኞች የውል ስምምነቱን አልፈፀሙም፡፡ ከአጠቃላይ ዕድለኞች 77 በመቶ የሚሆኑት ቁልፍ ለመረከብ የሚስችላቸውን ውል ፈፅመዋል፡፡

በተራዘነው ጊዜ ገደብ ውል የማይፈፅሙ ዕድለኞች በራሳቸው ጊዜ ቤቱን እንደማይፈልጉት ተቆጥሮ ዕድሉ እንደሚያመልጣቸው ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የተያዘና ወታደራዊ ግዳጅ ላይ የተሰማሩ አካላት ከተቀመጠው ጊዜ ገደብ በኋላም ሊስተናገዱ እንደሚችሉ ነው የተናገሩት፡፡

መንግስት 20/80፣ 10/90 እና 40/60 የቤት መርሀ ግብሮችን ነድፎ ለተጠቃሚዎች በዕጣ በማስተላለፍ የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡