በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ ለመንገድ መልሶ ማልማት ሥራ ከመኖሪያና ከመስሪያ ቦታቸው ለተነሱ 97 አባወራዎች 30 ሚሊዮን ብር ወጭ መደረጉ ተመለከተ፡፡
የከተማውን መንገድ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማስገንባት ከነዋሪዎቹ ጋር በመወያየት ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ መደረጉን የጅግጅጋ ከተማ ከንቲባ አቶ አህመድ መሀሙድ አህመድ ለዋልታ ተናግረዋል፡፡
ከቦታቸው ላይ ለሚነሱ ነዋሪዎች የመኖሪያና የንግድ ቤት የካሳ ክፍያና ለነዋሪዎቹ በተዘጋጀው አዲስ መንደር አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት 30 ሚሊዮን ብር ወጭ መደረጉን ከንቲባው አስረድተዋል፡፡
ነዋሪዎቹ በከተማው አቅራቢያ በተዘጋጀ መንደር እንዲሰፍሩ መደረጉን ከንቲባው ጠቁመው ነዋሪዎቹ ተገቢው ካሳ ተከፍሏቸው ፣የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተዘጋጅቶላቸውና በአዲሱ መንደር መሰረተ ልማት ተሟልቶ እንዲነሱ መደረጉን ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
በልማቱ ከተነሱት መካከል ወይዘሮ ዘውዲቱ ሰይፉ ቀደም ሲል በቀበሌ ቤት ይኖሩ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ከአካባቢያቸው መነሳታቸው የራሳቸውን ቤት እንዲኖራቸው መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ገልፀዋል፡፡ ‹‹ውሃ፣ መብራትና አስፈላጊው መሰረተ ልማት ተሟልቶልናል››ይላሉ፡፡
ወይዘሮ ኢናብ አህመድ በአዲሱ መንደር ትምህርት ቤትና ጤና ጣቢያ በመገንባቱ የሚፈልጉትን አገልግሎት በቅርበት እንደሚያገኙ ይገልፃሉ፡፡ ከቀድሞ አካባቢያቸው የተነሱት አምነውበትና ፈቅደው በመሆኑ ምንም ዓይነት ቅሬታ እንደሌላቸውም ጠቁመዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ከሌላ አካባቢ ለመጡ ዜጎች ተገቢውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ የሚናገሩት ደግሞ ወይዘሮ መሰረት ይንጋ ናቸው፡፡ በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት ወይዘሮ መሰረት የክልሉ መንግስት ከነዋሪዎች ጋር በመመካርና በመወያየት የሚያከናውነው ልማት የሚደነቅና የሚበረታታ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡
የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሀመድ ዑመር የክልሉ መንግስት ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ ሰሞኑን በጅግጅጋ ከተማ በተካሄደው 12ኛው ዙር የከተሞችና ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጉባዔ ላይ መናገራቸው ይታወቃል፡፡