ግቤ ሶስት በአማካይ 900 ሜጋዋት እያመነጨ መሆኑን ተቋሙ አስታወቀ

የግቤ ሶስት ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአማካይ 900 ሜጋ ዋት እያመነጨ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

1870 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ግቤ ሶስት በአሁኑ ወቅት በሙሉ አቅሙ ኃይል ማመንጨት ባለመጀመሩ 900 ሜጋ ዋት እያመነጨ እንደሆነ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የውጭ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ምስክር ነጋሽ ለዋልታ ገልጸዋል፡፡

የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ግንባታ 97 ነጥብ 5 የደረሰ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ውስጥም ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር አመልክቷል፡፡

1ነጥብ 5 ቢሊዮን ዩሮ የፈጀው የግቤ ሶስት ግንባታ እስከ 40 በመቶ የሚሆነው ወጭ በኢትዮጵያ መንግስት ቀሪው 60 በመቶ ደግሞ ከቻይና ኢንዱስትሪያል ኮሜርሻል ባንክ በተገኘ ገንዘብ  መሸፈኑን አቶ ምስክር አስገንዝበዋል፡፡

243 ሜትር ከፍታ ያለው ግድብ የግንባታ ጥራትና ደረጃው በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በጣም ተመራጭና ከፍተኛ ግፊትን የመቋቋም አቅም አለው ነው ያሉት፡፡

ግድቡ የተመረጠ የኮንክሪት መስሪያ ግብዓትን በከፍተኛ ጥግግት በመሙላት የሚገነባ የኮንክሪት ግንብ  ሲሆን ይህም ከተጠናው የውሃ ግፊት ባሻገር ያልተጠበቀ ተፈጥሮአዊ ክስተት ቢያጋጥም መቋቋም እንደሚችል ነው ያስረዱት ፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ግድቡ 6 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ኮንክሪት የተሞላ ሲሆን በግድቡ አማካኝነት በ210 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ በሚያርፈው ውሃ ትልቅ ሰው ሰራሽ ሃይቅ ይፈጠራል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱን 17ሺ ሜጋ ዋት ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል ፡፡