በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ የታቀደውን የሥራ ዕድል ፈጠራ ለማሳካት የሚረዳ የንቅናቄ መድረክ ይካሄዳል፡፡
የንቅናቄ መድረኩ በክልሉ በበጀት ዓመቱ የታቀደውን 878ሺ 455 የሥራ ዕድል ፈጠራ ለማሳካት ሰፊ ንቅናቄ ለመፍጠር ያግዛል ተብሏል፡፡
በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርጎ ነገና ተነገወዲያ የሚካሄደው የንቅናቄ መድረክ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንደሚመራ የክልሉ የቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ለዋልታ ገልጿል፡፡
በመድረኩ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች፣ ስኬቶችና ድክመቶች ተቀምረው እንደሚቀርቡ ተመልክቷል፡፡ የተሻለ ደረጃ ላይ የደረሱና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ኢንተርፕራይዞችም ምርጥ ተሞክሮዋቸውን ለሌሎች ያካፍላሉ፡፡
በክልል ደረጃ እስከ አሁን ድረስ ድረስ 137ሺ 889 የሥራ ዕድል መፈጠሩን የክልሉ የቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ በላይ ዘለቀ ተናግረዋል፡፡ አፈፃፀሙ 258ሺ 038 ለመፍጠር ከታቀደው አንፃር ሲታይ ዝቅተኛ መሆኑን አልሸሸጉም፡፡
አብዛኛው የሥራ ዕድል በማኑፋክቸሪንግ፣ በከተማ ግብርና፣ በንግድና በአገልግሎት ዘርፍ የተፈጠረ እንሆነም ከኃላፊው ማብራሪያ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በቀጣይ ዓመታዊ ዕቅዱን ለማሳካት የሚመለከታቸውን አካላት በማስተባበርና በማሳተፍ በትኩረት እንደሚሰራ አቶ በላይ ይናገራሉ፡፡ የንቅናቄ መድረኩም ለዚህ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡
የሁለቱን ቀናት የንቅናቄ መድረክ ተከትሎ በዞንና በወረዳ ደረጃ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ያተኮሩ የተለያዩ የንቅናቄ መድረኮች በስፋት እንደሚዘጋጁ ነው ምክትል ኃላፊው ያስረዱት፡፡ በጉዳዩ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትና ምክክር ይደረጋል፡፡
ነገ በሚጀመረው የንቅናቄ መድረክ ላይ የክልል ቢሮ ኃላፊዎች፣ የዞን አስተዳዳሪዎችና የመምሪያ ኃላፊዎችም፣ ከንቲባዎች፣ መንግስታዊ የሆኑና ያልሆኑ ተቋማት፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሴቶችና ወጣቶች በመድረኩ ይሳተፋሉ፡፡