ግንባታው የተጠናቀቀው 1870 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ግቤ ሶስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በይፋ ተመረቀ፡፡
ፕሮጀክቱ ዘመኑ የደረሰበትን የምህንድስና ጥበብ ተከትሎ የተገነባ፣ከአካባቢ ጋር ተስማሚና የአረንጓዴ ኢኮኖሚን መሰረት ያደረገና ፕሮጀክት መሆኑ ተመልክቷል፡፡
አገራዊ ዕድገትን ለማፋጠን የተነደፈውን ዕቅድ ለማሳካት ሚናው የጎላ መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተናግረዋል፡፡
ለሁለንተናዊ ዕድገትና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የኤሌክትክ ኃይል ወሳኝ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስት ጠቁመው ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግሩን ዕውን ለማድረግ የተያዘውን ጉዞ እንሚያፋጥን ገልፀዋል፡፡
ጊቤ ሶስት ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን በማልማት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን የመገንባት ጥረትን እየተከተለች መሆኑን ለዓለም ማሳያ እንደሆነም ነው የገለፁት፡፡
ከፋይናንስ ግኝትና ከመልክዓድር ጋር በተያዘ ከተለያዩ አካላት ሲቀርቡበት የነበረውን መሰረተ ቢስ ትችቶና ተግዳሮቶች ተቋቁሞ ለውጤት መብቃቱ የመንግስትና የህዝቡን ቁርጠኝነት ያመለካተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢኮኖሚያ ዕድገትን ተከትሎ የሚስተዋለውን የኃይል አቅርቦትና ክፍተት ለመሙላት የሚጫወተው ሚናም እጅጉን የጎላ እንደሆነ ነው ያመለከቱት፡፡ የአገር ውስጥ ፍላትን ከማሟላት ባሻገር ለጎረቤት አገራት ኃይል በማቅረብ በምስራቅ አፍሪካ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ማዕከል የመሆን ህልምን ዕውን የማድረግ ጥረት አጋዥ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የገጠሩን ህብረተሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡ ኃይልን ከማመንጨት በተጨማሪ የመነጨውን ኃይል በተገቢው መንገድ የማስተላለፍና የማሰራጨት ሥራው ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሥራ አስፈፃሚ ኢንጅነር አዜብ አስናቀ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን መሰረት አድርጎ የተገነባው ጊቤ ሶስት ኃይል ማመንጫ አሁን ያለውን የኃይል አቅርቦት 94 በመቶ እንደሚያሳድግ ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ጊዜው የደረሰበት ዘመናዊ የምህንድስና ጥበብን ተከትሎ የተመረጠ የኮንክሪት መስሪያ ግብዓትን በከፍተኛ ጥግግት በመሙላት የተገነባ የኮንክሪት ግንብ (ሮለር ኮምፓክትድ ኮንክሪት) መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ኢንጂነር አዜብ እንዳሉት ለፕሮጀክቱ ከአንድ ሚሊዮን ቶን በላይ ሲሚንቶ ሥራ ላይ ውሏል፡፡ ኃይሉን ወደ ብሔራዊ ቋት ለመውሰድ የሚያስችሉ እያንዳንዳቸው 300 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው 400 ኪሎ ቮልት የማስተላላፊያ መስመሮች ተዘርግተዋል፡፡
ሁለት የማከፋፈያ ጣቢያዎችም ተገንብተዋል፡፡ ከዘጠኝ ሺ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውን የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ በግብዓት አቅርቦትና በተለያዩ ዘርፎች ከ29 በላይ አገር በቀል ድርጅቶች ተሳትፈዋል፡፡
የሲቪል ሥራው በሳሊኒ ኢምፕሬ ጊሎ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራው በቻይናው ዶንግፋንግ ኤሌክትክ ኮርፖሬሽን የተከናወነ ሲሆን የግንባታ ቁጥጥርሩን የቻይናና ፈረንሳይ ኩባያዎች አከናውነዋል፡፡
እያዳንዳቸው 187 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችሉ 10 ተርባይኖች ዩኒቶች አሉት፡፡ ግንባታው አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዩሮ ወጭ የተደረገ ሲሆን 40 በመቶው በኢትዮጵያ መንግስት 60 በመቶ ደግሞ ከቻይና ኮሜርሻል ባንክ በተገኘ ብድር ነው የተሸፈነው፡፡
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለፕሮጀክቱ ዕውን መሆን ድጋፍ ላደረጉና በሥራው ላይ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ላበረከቱ አካላት የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል፡፡