ሜጋ ፕሮጀክቶች ችግሮችን በመጋፈጥ በተሻለ ደረጃ እየተፈጸሙ ናቸው -ጠቅላይ ሚኒስትር

የኢትዮጵያ ሜጋ ፕሮጀክቶች የተለያዩ ችግሮችን በመጋፈጥ የተሻለ አፈጻጸም እያሳዩ መሆናቸውን የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አስታወቁ ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ዛሬ በተካሄደው 12ኛ መደበኛ ስብሰባ የ11ኛውን መደበኛ ጉባኤላይ  ከህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ ሁሉም የሜጋ ፕሮጀክቶች አልዘገዩም ሁሉም ፕሮጀክቶችም አልተጓተቱም ነው ያሉት ፡፡

ከነዚሁም ውስጥ የባቡር ፕሮጀክት ሲታይ ከአዲስ አበባ ጁቡቲ የተዘረጋው 765 ኪሎሜትር መስመር በ4ዓመት ተኩል ውስጥ በርካታ ፈተናዎች በማለፍ መፈጸሙ በዓለም ደረጃ በጥቂቶች አገሮች ብቻ የሚከናወን ውጤታማ አፈጻጸም መሆኑን አስረድተዋል ፡፡

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡርም የተለያዩ ፈተናዎችን በማሸነፍ በአስደናቂ ሁኔታ በአጭር ጊዜ መፈጸሙን ነው የጠቀሱት ፡፡

በሀገራችን የተከናወኑ የመንገድ ፕሮጀክቶችም 82 በመቶ በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል ፡፡

ቀሪው 18 በመቶ የመንገድ ፕሮጀክቶች ደግሞ በተለያዩ የአፈጻጸም ችግሮች ምክንያት መጓተታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በአገር በቀል ኩባንያዎች ጭምር እየተከናወኑ የሚገኙ የሽረ እንዳስላሴ ፣የሀዋሳ፣የጂንካና የአርባ ምንጭ አየር ማረፊያዎች ባብዛኛው በተያዘላቸው ጊዜ እየተፈጸሙ መሆናቸውን ገልጸዋል ፡፡

ሌላው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 58 በመቶ መድረሱን የቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም 6ሺ ሜጋ ዋት ከታዳጊ አገር ዓቅም ጋር ሲታይ በታላቅ ቁርጠኝነት 24 ሰዓት  ሙሉ እየተሰራ የሚገኝ ፕሮጀክት መሆኑን አስገንዝበዋል ፡፡

ከውሃ በተያያዘ ከመሬት ውስጥ ከሚያጋጥም አስቸጋሪ የተፈጥሮ ፈተና እየተጋፈጡ የሚሰራ ስራ መሆኑን ያስገነዘቡት አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ፤የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ግን ደካማ መሆኑን ነው ያስታወቁት ፡፡

ይህም በዘርፉ በአገራችን ካሉ ባለሙያዎች ቁጥር እጥረት እና ከባለሙያዎች ዓቅም ማነስና የተያዘ መሆኑን ነው ያያስረዱት አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ፡፡

ይሁንና ከሁለት ዓመታት ወዲህ ግን ለባለሙያዎች የተሻለ ክትትልና የዓቅም ግንባታ ስልጠና ድጋፍ  እየተደረገላቸው የአፈጻጸም መሻሻሎች እየተታዩ መሆናቸውን ገልጸዋል ፡፡

በሀገራችን የተጀመሩት 10 የስኳር ፕሮጀክቶችም ሀገሪቱ ካላት የማስፈጸም ዓቅም ያላገናዘበ የተለጠጠ ዕቅድ በአንዴ በመጀመሩ የተያያዘ የመጓተት ችግር ማጋጠሙን ነው ያብራሩት ፡፡

ፕሮጀክቶቹ እየተገነቡበት ያሉት አከባቢዎችም መንገድ የሌላቸው ለተሽከርካሪና ለሰዎች እንቅስቃሴ አስቸጋሪ በመሆናቸው የተፈጠረ ችግር እንደነበርም አንስተዋል ፡

በተለይም በተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የተሰማራው የህንድ  ኩባንያዎች አፈጻጸምም ደካማና አስቸጋሪ እንደነበር አመልክተዋል ፡፡

ባንጻሩ በቻይናና በመከላከያ ብረታብረትና እንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የተያዙ  ኩራዝ ቁጥር አንድና በለስ ቁጥር አንድ የስኳር ፕሮጀክቶች በድፍረት የሚሰሩና በቅርቡ የሚጠናቀቁ ጥሩ አፈጻጸም የታየባቸው መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

በአጠቃላይ ሜጋ ፕሮጀክቶቻን ያለባቸውን ፈተና በመቋቋም አሁን ላይ ወደ ተሻለ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እየደረሱ በመሆናቸው መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚያከናውናቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አስታውቀዋል ፡፡

ዋልታ እንደዘገበው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በተለይም መንግስት የጀመረው የጥልቅ ተሃድሶ ሂደት የእስካሁኑ ውጤት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የአገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚ አፈፃፀምን፤ በጎሮቤት አገሮች የውጭ ግንኙነት የተመለከቱ ጥያቄዎች ላይ ሰፊ ማብራሪያዎች ሰጥተዋል  ።