በአዲስ አበባና በአምስት ክልሎች 3 ነጥብ 47 ቢሊዮን ሊትር ወተት ተመርቶ ለህብረተሰቡ ፍጆታነት መዋሉን የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ሚኒስቴር አስታወቀ ።
በሚኒስቴሩ የወተት ሃብት ልማት ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ ተካ እንደገለጹት፤ በግማሽ በጀት ዓመቱ ከአዲስ አበባ ከተማ ፣ ከትግራይ ፣ ከአማራ ፣ ከኦሮሚያ ፣ ከደቡብና ከቤኒሻንጉል ክልሎች 3 ነጥብ 47 ቢሊዮን ሊትር ወተት ተመርቶ ለህብረተሰቡ ፍጆታነት ውሏል።
በአገሪቱ የወተት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ ፓኬጆቹም ተግባራዊ መደረጋቸውን የገለጹት አቶ ታሪኩ ፤በተለይ 279 ሺ የሚደረሱ ለአርሶና አርብቶ አደሮች የኤክስቴንሽን አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል ።
እንደ አቶ ታሪኩ ገለጻ በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩም፤ አርብቶ አደሩና ወጣቱ የወተት ምርትን ለገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ምርቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል ።
በአገሪቱ የተሻለ የወተት ምርት የሚሠጡ የእንስሳት ምርጥ ዝርያዎችን የማዳቀል አገልግሎት የሚሠጠው አንድ ማዕከል ብቻ እንደነበር የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ በአሁኑ ወቅት ማዳቀያ ማዕከላት በመቀሌ ፣ በነቀምት በሐዋሳና በባህርዳር ከተሞች ተገንብተው አገልግሎት መሥጠት መጀመራቸውን አስታውቀዋል ።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ አንዲት ላም በቀን በአማካኝ 1ነጥን 37 ሊትር ወተት እየሠጠች መሆኗን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስቴሩ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከአንዲት ላም በአማካኝ በቀን የሚገኘው የወተት ምርት 6 ሊትር ለማድረሰ አቅዶ እየሠራ መሆኑን አቶ ታሪኩ አስረድተዋል ።
በኢትዮጵያ ከሏት 57 ሚሊዮን የቁም እንስሳት ውስጥ 10 ሚሊዮኑ ወተት የሚሠጡ መሆናቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።