የእንስሳትና አሳ ሃብት ሚኒስቴር 19ሺህ181 ቶን የዓሳ ምርት መገኘቱን አስታወቀ ።
በሚኒስቴሩ የዓሳ ሃብት ልማት ድህረ ምርት ባለሙያ አቶ አደፍርስ ካሳዬ ለዋልታ እንደገለጹት፤ባለፉት ስድስት ወራት 24ሺህ 822 ቶን ለማምረት ታቅዶ 19ሺህ 181 ቶን ዓሳ ማምረት ተችሏል ።
ሚኒስቴሩ የዓሳ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተለያዩ የአገሪቱ ሐይቆች፣ግድቦች ፣ወንዞችና ኩሬዎች ላይ የዓሳ ልማት ለማካሄድ ለአስጋሪዎች የተለያዩ ድጋፎች ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመዋል ።
ይህም የተለያዩ የጫጩት ማባዣ ማዕከላትን በመጠቀም ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በኦሮሚያ ፣ በደቡብና በአማራ ክልል 406 ሺ 787 የዓሳ ጫጩት ለአርሶና አርብቶ አደሮች እንዲሁም ለዓሳ አስጋሪዎች መሠራጨታቸውን ነው የገለጹት ።
በዓሳ ልማት ዘርፉ የህብረተሰቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ 8ሺ 572 አስጋሪዎችና አርሶአርብቶ አደሮችን በዓሳ ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ 12ሺ 732 ተጠቃሚዎች ማሳተፍ መቻሉን አቶ አደፍርስ አስረድተዋል ።
በተለያዩ የአገሪቱ አከባዎች ህገ ወጥ የዓሳ አስጋሪዎችን ለመከላከል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የምክክር መድረክ እያዘጋጀ ነው ያሉት አቶ አደፍርስ ህገወጥ የአሳ ማስገሪያ መሣሪያዎችን ለማስወገድ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል ።
ኢትዮጵያ በዓመት ከ90 ሺህ ቶን በላይ የዓሳ የማምረት ዓቅም ያላት ቢሆንም ፤ እየተመረተ የሚገኘው ምርት ግን ከ40 ሺህ ቶን አይበልጥም ነው ያሉት ።