የህዳሴው ዋንጫ በጉራጌና ስልጤ በነበረው ቆይታ 111 ሚሊዮን ብር ተሰበሰበ

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በጉራጌና በስልጤ ዞኖች በነበረው የአንድ ወር ቆይታ 111 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ምክር ቤት የህዝብ ተሳትፎ ማስተባባሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ ።      

የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አብርሃም ለዋልታ እንደገለጹት ፤ዋንጫው በጉራጌ ዞን በነበረው ቆይታ  ከህብረተሰቡ 60 ሚሊዮን  ብር  ከስልጤ  ዞን  ደግሞ  51 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል ።

በስልጤ ዞን የአገር ሽማግሌዎች  የህዳሴውን ዋንጫና ከብቶች ይዘው በመሄድ  ለጉራጌ ዞን ህዝብ  በስጦታነት ያበረከቱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ይህም ተግባር የሁለቱን ህዝቦች አንድነት ለማሳየትና ወዳጅነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ነው ያስረዱት ።    

የታላቁ ህዳሴ ዋንጫ  የብሔራዊ አንድነት  መገለጫ  መሣሪያ መሆኑንና ሁሉም የአገር  ዜጋ  ለታላቅ ፕሮጀክቱ ድጋፍ  የበኩሉን  አስተዋጽኦ እንዲያበረክት  የሚያግዝ መሆኑን አቶ ኃይሉ አብራርተዋል ።  

የህዳሴው ዋንጫ የብሔራዊ  አጀንዳዎችን ለማሳካትና በአገር ውስጥ  የይቻላል  መንፈስ እንዲሰርጽ  ታላቅ  ሚና እየተጫወተ  እንደሚገኝ አንሰተዋል ።

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ለአንድ ዓመት ያህል በኦሮሚያ ክልል በሁሉም ዞኖች  ቆይታው ካደረገ በኋላ ከወር በፊት ወደ ደቡብ ክልል የተለያዩ ዞኖች በመዘዋወር  ገቢ እያሰባሰበ ይገኛል  ነው ያሉት ።

እንደዚሁም የህዳሴው ዋንጫ በኦሮሚያ ክልል ቆይታው 607 ሚሊዮን ብር ፣ በአማራ ክልል  432 ሚሊየን ብር፣ በትግራይ ክልል 81 ሚሊዮን ብር  ፣ በአፋር  ክልል 71 ሚሊዮን ብርና በቤንሻንጉል ክልል 33 ሚሊዮን ብር ገቢ ማሰባሰብ መቻሉን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ጠቅሰዋል ።    

በአጠቃላይ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ከህብረተሰቡ ከ9 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡንም አስታውሰዋል  ።   

( ትርጉም : በሰለሞን ተስፋዬ )