አርሶአደሩ የግብርና ምርቱ ተገቢው ዋጋ እንዲያገኝ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የፌደራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ አስታወቀ ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ስሩር ለዋልታ እንደገለጹት ፤በ2008/09 ምርት ዘመን ከፍተኛ የግብርና ምርት በመገኘቱ ምክንያት የግብርና ምርት ዋጋ ወርዶ በአርሶ አደሩ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንዳያስከትል ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ።
በአገሪቱ የሚገኙ የመሠረታዊ ህብረት ሥራ ማህበራት አርሶ አደሩ የሰበሰበውን የሰብል ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ በመግዛት ለሸማቹ የህበረተሰብ ክፍል ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ እንዲቀርብ ለማድረግ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆኑን አስረድተዋል ።
ኤጀንሲው ከገዛው የሰብል ምርት ትርፍ የሆነውን ለኢትዮጵያ እህል ንግድ ድርጅት ፣ ለዓለም የምግብ ፕሮግራምና ለሌሎች አካላት ለመሸጥ ዝግጅት ማድረጉን ነው የጠቆሙት ።
በተጨማሪም የህብረት ሥራ ማህበራት የግብርና ምርትን ከሚያቀነባብሩ የተለያዩ የፓስታ፣ የዱቄትና የቢራ ፋብሪካዎች ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር የስንዴና የገብስ አምራች አርሶ አደሮች የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አቶ ኡስማን አስታውቀዋል ።
እንደ አቶ ኡስማን ማብራሪያ የህብረት ሥራ ማህበራት የሚያጋጥማቸውን የመጋዘን ችግር ለመፍታት በዘንድሮ የበጀት ዓመት 68 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ በተለያዩ ክልሎች ከ 5 ሺ ኩንታል በላይ የመያዝ አቅም ያላቸው መጋዝኖች ተገንብተዋል ።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 78 ሺህ 900 መሠረታዊ ህብረት ሥራ ማህበራት ፣373 የህብረት ሥራ ዩኒየኖች 17 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ካፒታል እያንቀሳቀሱ መሆኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።
ከዘንድሮ የመኸር ምርት 320 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ መገለጹ ይታወቃል ፡፡