በመቀሌ-ወልድያ-ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት እየተፋጠነ መሆኑን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ ፡፡
በመቀሌ-ወልድያ-ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት አጠቃላይ አፈጻጸምም 44 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ የአፈር ሙሌትና ቆረጣ ስራም 67 በመቶ መጠናቀቁን የፕሮጀክቱ ኃላፊ ኢንጂነር ገብረመድህን ገብረአሊፍ ገልጸዋል።
በፕሮጀክቱ እየተገነቡ ያሉ ትላልቅና መካከለኛ ዋሻዎች ግንባታቸው በሚቀጥሉት 5 ወራት እንደሚጠናቀቁ አስታውቋል።
እስካሁንም ቁፋሯቸው እየተከናወኑ ካሉ ስምንት ዋሻዎች ውስጥ እያንዳንዳቸው 2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው የሁለት ዋሻዎች ቁፋሮ መጠናቀቁን ገልጿል ።
ግንባታቸው የተጠናቀቀው የኮከሌ ዋሻዎች መሆናቸውን ኮርፖሬሽኑ ጠቁሟል ።
በዚህ የባቡር ፕሮጀክት ላይ ካሉት ዋሻዎች በርዝመቱ ቀዳሚ ሆኖ እየተቆፈረ ካለው 3 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የማይሰልፊ ዋሻ ውስጥ እስካሁን ከ2 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር በላይ መገባደዱን ነው ያመለከተው ።
የዚህ ዋሻ መጠናቀቅ ለፕሮጀክቱ መፋጠን ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ኢንጂነር ገብረመድህን አስረድተዋል።
ቀሪዎቹ ዋሻዎች ለመጠናቀቅ ከ20 እስከ 25 ሜትር ግንባታ ይቀራቸዋልም ነው ያሉት ።
ከእነዚህ ዋሻዎች ጎን ለጎን እየተገነቡ ካሉ 170 ድልድዮች ውስጥ 3 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን ጨምሮ በስምንት ወራት ግንባታቸው እንደሚናቀቁ አስታውቋል ።
የእነዚህ ትልልቅ ግንባታዎች መጠናቀቅ በአጠቃላይ የባቡር መስመር ግንባታው ላይ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ጠቁሟል።
እንደ ሃላፊው ገለጻ የድልድዮቹና የዋሻዎቹ ግንባታ መፋጠን እንዲሁም የአፈር ሙሌትና ቆረጣ ስራ አፈጻጸም ከፍተኛ መሆን ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ያስችለዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት በ1 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ በቻይናው ሲሲሲሲ ኩባንያ ግንባታው የተጀመረው የመቀሌ-ወልድያ-ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል-(ኤፍ.ቢ.ሲ)።