ሚኒስቴሩ ሥራ አጥ ወጣቶችን የመለየት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስታወቀ

በአገሪቱ የሥራ አጥ ወጣቶችን የመለየት ሰፊ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ ።

በሚኒስቴሩ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ናስር ለገሰ ለዋልታ እንደገለጹት በአገሪቱ የወጣቶች የሥራ አጥነትን ችግር ለማስወገድ የሚያስችለውን የወጣቶች የተንቀሳቃሽ ፈንድ ጥቅም ላይ ለማዋል ከወረዳ ጀምሮ የሥራ አጥ ወጣቶችን የመለየት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ። 

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በአገሪቱ የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለማስወገድ   በከተማና በገጠር በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሥራ ፈጠራ ለማበረታታት የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች እያካሄዱ መሆኑን አቶ ናስር ተናግረዋል ።

የአገሪቱ ወጣቶች ስኬታማ የሚያደርጓቸውን የሥራ መስኮች በመለየትና  የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች በአሁኑ ወቅት እየተሠጣቸው መሆኑ ተመልክቷል ።

በመላ አገሪቱ እየተካሄዱ ባሉት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች የተለያዩ የወጣቶች አደረጃጀቶች በወጣቶች የዕድገትና የለውጥ ፓኬጅና የወጣቶች ስትራቴጂዎች ላይ  በመወያያት መግባባት ላይ ለመድረስ ውይይት እያካሄዱ  ይገኛል ተብሏል ።

ወጣቶች ከተንቀሳቃሽ ፈንዱ ተጠቃሚ የሚሆኑት ለሚሠማሩበት የሥራ መስክ የሚውለውን 10 በመቶ ገንዘብ በጋራ በመሆን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲቆጥቡ መሆኑን አቶ ናስር  ጠቁመዋል ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች ቀሪውን  የብድር ገንዘቡን ከንግድ ባንክ ማግኘት እንደሚችሉ የሚገልጹት አቶ ናስር  የንግድ ባንክ በማይገኙባቸው የገጠር አካባቢዎች በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ብድር ይመቻችላቸዋል ብለዋል ።

በገጠርና በከተማ የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶች ቢያንስ አምስት ሆነው በመደራጀት አዋጭ  በሆኑ የሥራ ዘርፎች ለመሠማራት የራሳቸውን ፕሮጀክት በመቅረጽናበማቅረብ መንግሥት  በዘንድሮ የበጀት ዓመት ከመደበው የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ተመልክቷል ።

በአገሪቱ የሚገኙ ወጣቶች በመንግሥት  የቀረበውን  የተንቀሳቃሽ  ፈንድ  በመጠቀም በተለያዩ  አማራጭ የሥራ መስኮችን ላይ በመሠማራት  የራሱን የኢኮኖሚያዊ አቅም ከማሳደግ ባለፈ  ለአገር ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት አቶ ናስር ጥሪ አቅርበዋል ።