ባለሥልጣኑ በ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ አምስት የመንገድ ግንባታዎችን ለማከናወን የኮንትራት ስምምነቶችን ፈጸመ

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በአጠቃላይ በ5 ቢሊዮን ብር ወጪ አምስት የመንገድ ፕሮጀክቶችን  ለማከናወን  የኮንትራት ስምምነቶችን ፈጸመ ።

አምስቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ 357 ኪሎሜትር እርዝማኔ ያላቸው ሲሆን  መንገዶቹም የጭዳ -ሶዶ ሶስተኛ ኮንትራት ፣  የጨርቲ -ጎርቦክሳ- ጎሮዳሜ ፣ የፊቅ -ሀመሮ -ኢሚ ኮንትራት አንድ ፣የጊኒጪ-ካቺሴ -ጩሉቲ ኮንትራት አንድ እና የፓዊ መገንጠያ-ህዳሴ ግድብ ናቸው ።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ግርማይ በፊርማ ስነ ሥርዓቱ ወቅት እንደገለጹት በዘንድሮ የበጀት ዓመት ባለሥልጣኑ ግንባታቸውን ለማስጀመር ካቀዳቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል የትናንትናውን ጨምሮ በአጠቃላይ በ13ነጥብ7 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚከናወኑ 18 ፕሮጀክቶች ለአሸናፊ ድርጅቶች ተሠጥተዋል ብለዋል ።

የመንገድ ፕሮጀክቶቹ  ግንባታ የሚካሄዱት ከዚህ ቀደም ምንም  የመሠረተ ልማት  ባልነበረባቸው አከባቢዎች  በአስፓልት ደረጃ የሚገነቡ  በመሆኑ በተለያዩ  አካባቢዎች ለህብረተሰቡ  ኢኮኖሚያዊና  ማህበራዊ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል ።

የጭዳ -ሶዶ የ 58 ኪሎሜትር የመንገድ ፕሮጀክትን ለማካሄድ ጨረታውን ያሸነፈው ኢንቨስትስትሮይፕሮኤክትሊ ሊሚቲድ  ኩባንያ የተባለ የሩሲያ  አለም አቀፍ የሥራ ተቋራጭ ሲሆን  መንገዱ በአጠቃላይ   1 ቢሊዮን  171  ሚሊዮን ብር  በሆነ ወጪ  በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ  ግንባታው አጠናቆ ለማስረከብ ተስማምቷል ።

የጨረቲ- ጎሮቦክሳ- ጎሮዳሜ  የ90 ኪሎሜትር እርዝመት ያለውን የመንገድ ፕሮጀክት  ግንባታ በ1ቢሊዮን  300  ሚሊዮን  ብር  ለማከናወን ከባለሥልጣኑ ጋር ስምምነት የፈጸመው   ሲሲሲሲ  የተባለ የቻይና ዓለም አቀፍ  የመንገድ የሥራ ተቋራጭ  ሲሆን  ግንባታው ለማጠናቀቅ የሦስት ዓመት ጊዜ  ተሠጥቶታል ።

ሌላው በትናንትናው ዕለት የኮንትራት ስምምነት የተፈጸመው 81 ኪሎሜትር እርዝመት ያለው የፊቅ -ሐመሮ- ኢሚ  ኪሎሜትር  የመንገድ ፕሮጀክት ነው ።

የመንገድ  ግንባታውን በ 819 ሚሊዮን ብር 129 ሺ ብር ለማከናወን  ባለሥልጣኑን ያወጣውን ጨረታ ያሸነፈው ማክሮ ጀነራል ኮንትራክተርስ የተባለ አገር በቀል የመንገድ ሥራ  ተቋራጭ ሲሆን  የመንገድ ግንባታው   በሦስት ዓመት  ጊዜ ውስጥ  ሙሉ ሙሉ አጠናቆ ለማስረከብ ውል ፈርሟል ።

ሌላው   ባለሥልጣኑ   ግንባታው ለማስጀመር  የውል ስምምነት  የፈጸመበት  የ 59 ኪሎሜትር እርዝማኔ ያለው የጊኒጪ-ካቺሴ-ጩለቲ  የመንገድ ፕሮጀክት  በፊርማው ወቅት  ተገልጿል  ።

ፕሮጀክቱን  በ 846 ሚሊዮን 273 ሺ ብር  ወጪ  ለማከናወንና  ግንባታው በ 33 ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ  የተስማማው   ገምሹ  በየነ ኮንስትራክሽን የተባለ አገር በቀል  ድርጅት መሆኑ  በፊርማ ሥነሥርዓቱ ወቅት ተገልጿል ።

በመጨረሻም ባለሥልጣኑ የፓዌ መገንጠያ-ህዳሴ ግድብ የ69 ኪሎሜትር የመንገድ ግንባታን  በ887 ሚሊዮን 759 ሺ  ብር ለማከናወን  ካሸነፈው የቻይና ሬል ዌይ ቁጥር ሦስት ዓለም አቀፍ ተቋራጭ ጋር የስምምነት ፊርማውን አድርጓል ።

ተቋራጩም  የመንገድ ፕሮጀክቱን በሦስት ዓመት ለማስረከብ ተስማምታል ።

የኢትዮጵያ  መንገዶች ባለሥልጣን  በአሁኑ ወቅት የ339 የመንገድ ግንባታና የጥገና  ፕሮጀክቶችን እንዲሁም  የ94  የመንገድ ፕሮጀክቶችን አዋጭነት ፣ የዲዛይን እና የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ እያደረገ መሆኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።