የክልል ተሳታፊዎች ባዛሮች የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደረዷቸው ገለጹ

የሀገር አቀፉ የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ኤግዚቢሽንና ባዛር የገበያ ተስስር ለመፍጠር ምቹ አጋጣሚ እንደሆኑላቸው ከተለያዩ ክልሎች የመጡ የባዛሩ ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡

ከተሳታፊዎቹ መካከል ከአርባምንጭ እንደመጣ የገለጸልን ወጣት አስራት ካሳ በሕዳሴ የሞሪንጋ ማቀነባበሪያ እንደሚሰራና በተለይም ተመሳሳይ የኤግዚቢሽንና ባዛር መድረኮች መዘጋጀታቸው የገበያ ትስትስ ለመፍጠር፣ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅና በስፋት ለመሸጥ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ብሏል፡፡

መድረኩ በተለይም ለክልል ኢንዱስትሪዎች ወደ መሀል ከተማ መጥተው እንዲሰሩ የሚፈጥረው ዕድል ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነም አስራት ጠቁሟል፡፡

ኤልሳቤጥና ታደለ የቆዳ ውጤቶች የሕብረት ሽርክና ማሕበር ባለድርሻ ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ፍቅሬ በበኩሏ ቀደም ሲል በ2ሺህ ብር የተመሰረተው ማህበራቸው አሁን ላይ ካፒታሉን ወደ 1.5 ሚሊየን ብር በማሳደግ ወደ መካከለኛ ኢንትርፕራይዝነት ከመሸጋገሩም ባሻገር ምርት ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ለመላክም ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ ተናግራለች፡፡ ማሕበሩ ለ22 ሰራተኞችም የሥራ እድል መፍጠር እንደቻለም ተመልክቷል፡፡

የማምረቻ ቦታ እጥረት ግን በስፋት ለማምረት እክል እንደሆባቸው ወይዘሮ ኤልሳቤጥ አክላ ገልጻለች፡፡

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ በተለይም የገበያ ትስስር በመፍጠርና የሚሰራበት ፋብሪካ አዲስ እንደመሆኑ ምርቱን ለማስተዋወቅ መልካም ዕድል እንደፈጠረለት የነገረን ደግሞ የባህርዳሩ የዩኒክ የማካሮኒ ፋብሪካ የሽያጭ ባለሙያ እዮብ አዱኛ ነው፡፡

የባሕል ልብሶችን በተለይም በትግራይ ክልል የሚለበሱ የፈትል ልብሶችን ይዛ ኤግዚቢሽንና ባዛሩን የተቀላቀለቸው የአድዋዋ ወይዘሮ አብረኸት በርሄ በበኩሏ ኤግዚቢሽኑና ባዛሩ የክልሉን ባሕላዊ አልባሳት ለማስተዋወቅና ከአከፋፋዮች ጋር በቀጣይ በጋራ ለመስራት እንደስቻላት ገልጻለች፡፡

የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ ልማት ኤጀንሲ የሀገር ውስጥ ገበያ ልማት ቡድን መሪ የሆኑት አቶ መልካም ጌታሁን የሀገር አቀፉ ኤግዚቢሽንና ባዛር በጥርና ግንቦት ወራት እንደሚካሄድና በዚህም በተለይ ከክልል የሚመጡ ኢንተርፕራይዞች ተሳትፏቸው እየጎላ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ ኤጀንሲው ለኢንዱስትሪዎች ልማት በሰጠው ትኩረትም አስከ 5 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ በማድረግ በተለይም የወጣቶችን ተጠቃሚነትና የሥራ እድል ፈጠራ ለማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡

በኤግዚቢሽንና ባዛሩ 109 ኢንትርፕራይዞችና 21 ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ እንደሆነ ታውቋል፡፡

በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ላይ ከአፋርና ሶማሌ ክልሎች በስተቀር በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እየተሳተፉ እንደሆነ አቶ መልካም አያይዘው ገልጸዋል፡፡

ጥር 22 በድምቀት የተከፈተው ኤግዚቢሽንና ባዛር አስከ ጥር 28 2009 ድረስ እንደሚቆይ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡