የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመንግስት ሠራተኞች የደመወዝ ማስተካከያና የጡረተኞች አበል ጭማሬ ከጥር 1 ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆኑ ውሳኔ አሳለፈ።
የሚኒስትሮች ምክር ቤቱ ዛሬ 22ኛ መደበኛ ስብሰባ አካሂዷል።
በስብሰባው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽንን ለማቋቋም በተዘጋጀ ረቂቅ ደንብና ኢትዮጵያ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በተስማማችባቸው የብድር ስምምቶች ላይም ውሳኔዎችን አሳልፏል።
ምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ ለመንግስት ሠራተኞች የደመወዝ ማስተካከያ እንደሚደረግ ቃል በተገባው መሰረት ተጠንቶ የቀረበለትን ማስተካከያ ተግባራዊ እንዲሆን ወስኗል።
የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ለመንግስት ሠራተኞች ደመወዝ ማስተካከያ በተመለከተ ባቀረበው ጥናት ላይ ምክር ቤቱ ከተወያየ በኋላ ነው ከጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን የወሰነው።
በተጨማሪም በመንግስትና በግል ሠራተኞች ጡረተኞች የአበል ጭማሪ ላይ ከተወያየ በኋላ ከጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን መወሰኑን መግለጫው አመልክቷል።
የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲን የአደረጃጀት፣ የአሰራርና የሰው ኃይል ችግሮችን በመፍታት ተቋሙ ተልዕኮውን በውጤታማነት ለመፈጸም እንዲችል ጥናት መደረጉን መግለጫው አመልክቷል።
በገበያ ሂሳብ ቤቶች የማልማት፣ የማከራየት፣ የመጠገንና የማስተዳደር ተልዕኮ ያለው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ መቅረቡንም አትቷል።
ምክር ቤቱ በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ ማሻሺያዎችን በመጨመር ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እንዲወጣና በሥራ ላይ እንዲውል መወሰኑንም መግለጫው ያሳያል።
ኢትዮጵያ በመስኖ ልማት፣ መጠጥ ውኃ፣ መንገድ ግንባታ፣ በኤሌትሪክ አገልግሎት እንዲሁም በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት ጋር ያደረገቻቸውን የብድር ስምምነቶች በተመለከተ መወያየቱ ተመልክቷል።
ምክር ቤቱ ከአገሪቷ የብድር ስምምነቶች ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን ተቀብሎ ይጸድቁ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ መወሰኑንም መግለጫው ያመለክታል።(ኤዜአ)