በክልሉ 164ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት ይጠበቃል

በኦሮሚያ ክልል በ2008/9 የመኸር ወቅት በአጠቃላይ 164 ነጥብ6 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የክልሉ የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ቢሮ አስታወቀ ።

የኦሮሚያ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ የኮሚኒኬሽን የሥራ ሂደት መሪ አቶ ተሰማ ገብረመድን ለዋልታ እንደገለጹት በዘንድሮ የመኸር ወቅት በክልሉ 6ነጥብ08 ሄክታር መሬት በሰብል የተሸፈነ መሆኑንና እስካሁን ድረስ 5ነጥብ7 ሄክታር መሬት ላይ የሚገኘው ሰብል ተሰብስቧል ብለዋል ።

በኦሮሚያ ክልል በአብዛኛው አካባቢዎች የሰብል ምርቱ እንዲሰበሰብ መደረጉን የጠቆሙት  አቶ ተሰማ በአንዳንድ ደጋማ አካባቢዎች ፣በባሌና በጉጂ ዞን የምርት ማሰባሰብ ሥራው በሁለትሳምንታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል ።

ባለፈው ዓመት የመኸር ወቅት በአጠቃላይ በክልሉ ከ5ነጥብ9 ሚሊዮን ሄክታር በሰብል ዘር  ተሸፍኖ 133 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል ምርት መገኘቱን ያስታወሱት አቶ ተሰማ  በዘንድሮ ዓመት ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ሥራዎች በመከናወናቸው የተሻለ ምርት እንደሚጠበቅ አስረድተዋል ።

በክልሉ የአርሶ አደር የግብርና ቴክሎጂዎችን እንዲጠቀሙ፣ አሠራሮችን እንዲተገብሩና  የተለያዩ የግብርና ግብዓቶች በበቂ ሁኔታ እንዲቀርብ መደረጉን የገለጹት አቶ ተሰማ  የባለሙያ፣ ድጋፍና ክትትል ለዘንድሮ ምርት ማደግ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል ።

በክልሉ በተለይ ድንገተኛ  ዝናብ  ሲያጋጥም የሰብል ምርቱን  በመሰብሰብ በኩል ከአርሶ አደሩና የአርሶአደሩ ቤተሰብ በተጨማሪ ፣ የክልሉ ተማሪዎች ፣ የመንግሥት ሠራተኞችና የመከላከያ ሠራዊት አባላት  መሳተፋቸውን አቶ ተሰማ  አያይዘው ገልጸዋል ።

በኦሮሚያ ክልል የግብርና ምርቱን ይበልጥ ለማሳደግ  በክልሉ በሚገኙ 287 ወረዳዎች ከጥር 1 ጀምሮ ለሁለት ወራት የሚቆይና 11 ሚሊዮን  ህዝብን የሚያሳትፍ የተፋሰስ ልማት የዘመቻ  ንቅናቄ  እንደሚካሄድ ዋልታ ኢንፎሜሽን ማዕከል  ዘግቧል ።