የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተቀማጭ ገንዘቡ 320 ቢሊየን ብር መድረሱን አስታወቀ፡፡
ባንኩ ሰኔ 2008ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ጠቅላላ ሐብቱ 288 ቢሊየን 460 ሚሊየን የነበረ ሲሆን በስድስት ወር ውስጥ ካፒታሉን በ31 ነጥብ 54 ቢሊየን ብር ማሳደግ እንደቻለ የባንኩ የኮሙዩኒኬሽን ክፍል ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጅ አቶ በልሁ ተክሉ ለዋልታ ገልጸዋል፡፡
የገንዘቡ መጠን ከፍ እንዲል የሕብረተስቡ የቁጠባ ባሕል እየተሻሻለ መምጣቱ ጉልህ ሚና እንዳለው ታውቋል፡፡
ሕብረተሰቡ በተለይም በጋራ ቤቶች ቁጠባ እያደረገ ያለው ተሳትፎ ከፍተኛ እንደሆነ አቶ በልሁ ገልጸዋል፡፡
በ10/90 የቤቶች ቁጠባ ፕሮግራም 23ሺህ664 እንዲሁም በ20/80 ፕሮግራም ደግሞ 696ሺህ 451 ዜጎች ያለማቋረጥ እየቆጠቡ ነው፡፡
ባንኩ ሐብቱን በየጊዜው ማሳደግ በመቻሉ ለአዋጪ የኢንቨስትመንት ፕሮጄክቶች የማበደር አቅሙም እየተሻሻለ መምጣቱን አቶ በልሁ አክለው ገልጸዋል፡፡
በዚህ መሰረት ባሳለፍነው ስድስት ወር ለግሉ ሴክተር ብቻ 11 ቢሊየን ብር በላይ ማበደር ተችሏል፡፡
ባንኩ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ያሉ ጠቅላላ ቅርንጫፎቹ ከ1ሺህ 170 በላይ ደርሷል፡፡
ከኢትዮጵያ ውጪም በደቡብ ሱዳን ቅርንጫፍ ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን በጅቡቲና ሰሜን ሱዳንም አዳዲስ ተጨማሪ ቅርንቻፎችን ለመክፈት ቅድመ ዝግጅቶችን እያጠናቀቀ ነው፡፡