ሶላር ኪዮስክ የፀሃይ የኃይል መሣሪያዎችን በአገሪቱ የገጠር አካባቢዎች ለማስፋፋት እየሠራ ነው

ዓለም አቀፉ የፀሃይ ኃይል ምንጭ መሣሪያዎች አቅራቢ ኩባንያ የሆነው ሶላር ኪወስክ ሶሉሽንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ በኢትዮጵያ የተለያዩ የገጠር አካባቢዎች የፀሃይ ኃይል ምንጭ  መሣሪያዎች በስፋት በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ገለጸ ።       

የኩባንያው የአገር ውስጥ የማስፋፊያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሃኒባል ገብረመድህን ለዋልታ እንደገለጹት ኩባንያው የፀሃይ የኃይል ምንጭ መሣሪያዎችን በበቂ መጠን ለማቅረብ  በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች  23 ሱቆችን ከፍቷል ።

ኩባንያው በተለያዩ አካባቢዎች የሚያቀርባቸው የፀሃይ ኃይል ምንጭ መሣሪያዎች ለማባዣ ማሽኖች ፣ ለሞባይል ቻርጀር፣ ለቴሌቪዠንና ለሌሎች እቃዎች  አገልግሎት መሥጠት የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል ።         

ኩባንያው ከአውሮፓ ህብረት ባገኘው ድጋፍ 40 ተጨማሪ የመሸጨያ ሱቆችን  በመክፈት  አገልግሎቱን ለማስፋት  እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል ።

 ኩባንያው ከሚከፍታቸው 40 ከሚሆኑት አዳዲስ ሱቆች ውስጥ ሦስቱ ባለፈው ሳምንት በባሌ ኳሶ ማንሶ አካባቢ  ሥራ መጀመራቸውን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል ።      

በአንዳንድ አካባቢዎች ኩባንያው ያቀረባቸው መሣሪያዎች የፀጉር ቤትና የዲኤስ ቲቪ ቴሌቭዥን ማሳያ አገልግሎትን ለመሥጠት ማስቻሉን  የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ  ኩባንያው  በአፍሪካ  በኬንያ ፣ ታንዛኒያ ፣ ማዳጋስካርና ረዋንዳ መሣሪያዎችን እያቀረበ ነው ብለዋል ።  

ከሶላር ኪውስክ ሶሉሽንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያው የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው ኩባንያው እስካሁን  ባቀረባቸው የፀሃይ ኃይል  መሣሪያዎች 17ሺ ቤተሰቦች ተጠቃሚ መሆን የቻሉ ሲሆን በገጠር ጥቅም ላይ የማለውን ማሾን በመተካት ላይ ይገኛል ።  

በኢትዮጵያ  የኤሌክትሪክ ኃይል  ባልተዳረሰባቸው የገጠር አካባቢዎች  የፀሃይ ኃይል ምንጭን  የሚጠቀም የህዝብ ቁጥር እያደገ መጥቷል ።

( ትርጉም : በሰለሞን ተስፋዬ )