በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የአካባቢ ተጽዕኖ ጥናትና ግምገማ የሚያካሄዱ አማካሪ ድርጅቶች የሚወክላቸውን ማህበር ማቋቋም እንደሚገባቸው የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር አስታወቀ ።
በሚኒስቴሩ የአካባቢ ጥበቃ ፈቃድ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙሉብርሃን ታሪኩ እንደገለጹት በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የአካባቢ ተጽዕኖ ጥናትና ግምገማ የሚያካሄዱ ድርጅቶች ማህበር እንዲያቋቋሙ ያስፈለገው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያወጣቸውን ህግና ደንቦች ለማህበሩ ለማሳወቅና በቀላሉ ከድርጅቶቹ ጋር ግንኙነቶችን ለመፍጠር እንዲያሰችል ነው ።
በአካባቢ ጥበቃ ላይ የተሠማሩት ድርጅቶች የሚክሉት አንድ ማህበርን በመጠቀም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በወቅታዊ የአካባቢ ጥበቃ የአሠራር ሁኔታዎች ላይ መመካከርና መወያየት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር እንደሆነ ወይዘሮ ሙሉብርሃን ተናግረዋል ።
እስካሁን በአገሪቱ 52 የሚደርሱ ድርጅቶች በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተመዘገቡ የአካባቢ ጥበቃ ድርጅቶች እየተንቀሳቀሱ ሲሆን በሥራቸው ስምንት የአካባቢ ጥበቃ አማካሪወችን ማቋቋም ችለዋል ።
በአገሪቱ የአካባቢ ጥበቃ አዋጅ መሠረት ማንኛውም በአካባቢ ጥበቃ ሥራና የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ሥልጠና ያገኘ ግለሰብ በቅፉ ያለውን ልምድ በማቅረብ የአካባቢ ጥበቃ አማካሪ ፈቃድን ማግኘት እንደሚችል ወይዘሮ ሙሉብርሃን አያይዘው ገልጸዋል ።
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባትና እኤአ በ2025 ተግባራዊ ለማድረግ ያስቀመጠችውን ግብ ለማሳካት በአገር ውስጥ እየተንቀሰቀሱ የሚገኙ የአካባቢ ጥበቃ ድርጅቶችና አማካሪዎች የበኩላቸውን ሚና ይጫወታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።
( ትርጉም: በሰለሞን ተስፋዬ)