በድሬዳዋ የአፈር መሸርሸር 27 በመቶ መቀነሱን ቢሮው ገለጸ

በድሬዳዋ አስተዳደር በተካሄዱ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የአፈር መሸርሸር  አደጋ 27 በመቶ መቀነሱን የግብርና ውሃ ፣ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ገለጸ ፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ኑረዲን ዓብደላ ዛሬ ለዋልታ እንደገለጹት፤ ከ2004 አንስቶ እስከ ባለፈው ዓመት ድረስ በተካሄደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ዘመቻ በአከባቢው ይደርስ የነበረው የአፈር መሸርሸር አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል ፡፡

ከዚህ በፊት በአከባቢው በሚዘንበው ዝናብ የአፈር መሸርሸሩ 75 በመቶ የነበረ ሲሆን ፤አሁን ግን ወደ 48 በመቶ መውረዱን ነው ያስረዱት ፡፡

በዚሁም የሚዘንበው ዝናብ መሬት ውስጥ እየሰረገ የከርሰ ምድር ውሃ ከማጎልበቱም ባሸገር ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

ከዚህ በፊት መስኖ ያልነበረባቸው ቦታዎች መስኖ መጀመሩን አብራርተዋል ፡፡

የከርሰ ምድር ውሃ በቅርብ ርቀት እየተገኘ መሆኑንም ጠቁሟል ፡፡

ዘንድሮም የአፍርና ውሃ ጥበቃ ስራ አጠናክረው በመቀጠል በቀን 45 ሺ ህዝብ በማሳተፍ በ3ሺ 678 ሄክታር መሬት ላይ ስራው ለማካሄድ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ኃላፊው አስታውቀዋል ፡፡

ይህም በአከባቢው በሄክታር 4ነጥብ 3 በመቶ የአፈር መሸርሸርን ይቀንሰዋል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል ፡፡