የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በዛሬው ዕለት በሚሊኒየም አዳራሽ በተከፈተው 15ኛው የአፍሪካ የቡና ጉባኤና ኢግዚቢሽን ላይ እንደተናገሩት መንግሥት ወደ ውጪ የሚላከውን የቡና ምርት በማሳደግ ፣ የቡና ላኪዎችና ሌሌች የቡና ምርት ባለድርሻ አካላት ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ድጋፍ ያደርጋል ።
ዶክተር ሙላቱ በንግግራቸው ኢትዮጵያ ለቡና ምርት እጅግ ተስማሚ ከፍታ ፣ ሙቀትና የአፈር ለምነት ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው አገሪቱ በቡና ብዝሃ ህይወት የበለጸገች መሆኗ የቡና ምርቷን ይበልጥ ለማሳደግ ይረዳታል ብለዋል ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በቡና ዋጋ መውረድ ምክንያት ባለፉት አምስት ዓመታት አገሪቱ ወደ ውጪ የምትልከው የቡና መጠን እያደገ ቢመጣም ከቡና ዘርፍ የምታገኘውን ገቢ መቀነሱን ፕሬዚደንቱ ሙላቱ ጠቁመዋል ።
የአፍሪካ ፋይን ኮፊ ማህበር ሊቀመንበር የሆኑት አብዱላህ ባጋርሽ በበኩላቸው እንደገለጹት የአፍሪካ ፋይን ኮፊ ጉባኤ ኢግዚቢሽን በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ እውቅና ካላቸው ሦስቱ ጉባኤዎች መካከል የሚመደብ መሆኑንና የአፍሪካን የቡና እንዱስትሪ ለውጭ ዓለም ይበልጥ ሊያስተዋወቅ የሚያስችል ነው ብለዋል ።
በተጨማሪም የአፍሪካ ፋይን ኮፊ ጉባኤን ማካሄድ ለአፍሪካውያን የቡና አቅራቢዎች የንግድ ግንኙነት እንዲፈጥሩ የሚያስችልና ዓለም አቀፍ የቡና ምርት ገዢ ኩባንያዎች የአትዮጵያንም ሆነ አፍሪካን የቡና ጣዕም አውቀው ለቀጣይ ሥራ እንዲዘጋጁ የሚያግዝ መሆኑን አብዱላህ ባጋርሽ አመልክተዋል ።
በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከቡና ምርቱን ህይወታቸው የተቆራኘ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን የቡና ኢንዱስትሪው ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነው እንደሚሸፍን መረጃዎች ይጠቁማሉ ።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የቡና አምራች አገር ስትሆን በዓለም በቡና ምርት የ5ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝና በአጠቃላይ ከ7 እስከ 10 በመቶ የዓለም የቡና ምርት ከኢትዮጵያ ይገኛል ።
በ15ኛው የአፍሪካ ፋይን ኮፊ ጉባኤና ኢግዚቢሽን ከ 2ሺህ በላይ የአፍሪካ ልዑካን ፣ ዓለም አቀፍ የቡና አዘጋጆች ፣ አምራቾች ና ዓላም የተውጣጡ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል ።
በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄደው 16ኛው የአፍሪካ ፋይን ኮፊ ጉባኤና ኢግዚቢሽን አዘጋጅ ኡጋንዳ መሆኗ ታውቋል ።