ሚኒስቴሩ ከ40 በመቶ በላይ የእርሻ መሬት ለበልግ ምርት መዘጋጀቱን አስታወቀ

በአገሪቱ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነው የሚታረስ መሬት ለበልግ ወቅት እርሻ ዝግጁ እንዲሆን መደረጉን የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አስታወቀ ።   

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ብርሃኑ ለዋልታ እንደገለጹት በአገሪቱ በአጠቃላይ ከሚታረሰው መሬት ውስጥ 40 በመቶ የሚሆነውን መሬት  ለበልግ ወቅት  የሰብል ምርት  ዝግጁ  እንዲሆን  የማድረግ  ሥራዎች  ተከናውነዋል ።   

ኢትዮጵያ ለበልግ ወቅት ምርት የሚያስፈልጋትን  1ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ  ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ወደ የተለያዩ  ክልሎች  እንዲሰራጩ መደረጉን  አቶ አለማየሁ  ተናግረዋል ።

አርሶ አደሩ በበልግ ወቅት የውሃ እጥረት እንዳያጋጥመው  ከወዲሁ  ውሃን  መቆጠብ የሚያስችሉ ጥንቃቄዎችን ሲያደርግ መቆየቱን  የገለጹት  አቶ አለማየሁ ውሃን  በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችሉ ዘዴዎችን  አርሶአደሩ እንዲያውቃቸው ተደርጓል ብለዋል ።            

የአፈር እርጥበትን  ማቆየት  የሚያስችሉ  የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን አርሶ አደሩ በስፋት  እንዲጠቀም  የግብርና ኤክስቴንሽን  ባለሙያዎች  ድጋፍ  ሲያደረጉም  መቆየታቸውን አቶ አለማየሁ አያይዘው ገልጸዋል ።

በተለይ  በደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች  በዘንድሮ   የበልግ ወቅት የአነስተኛና መካከለኛ የመስኖ የልማት ሥራዎች ይበልጥ  እንዲካሄዱ  ትኩረት  የተሠጠው ተግባር  መሆኑን  አቶ  አለማየሁ ጠቁመዋል ።  

የእርሻና  ተፈጥሮ ሃብት  ሚኒስቴር  ምርትና ምርታማነትን  ለማሳደግ ጎን ለጎን  የአገሪቱን የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ዓላማውን  ስኬታማ ለማድረግ  አርሶአደሩ  የእንስሳትና አሳ እምቅ  ሃብቱን ይበልጥ ጥቅም ላይ እንዱያውል  ከእንስሳትና አሳ ሃብት  ልማት ሚኒስቴር ጋር ተቀናጅቶ እንደሚሠራ  አመልክቷል ።

ሃምሳ በመቶ የሚሆነው  የደቡብ ክልልና ከ30 በመቶ በላይ  የሚሆነው  የኦሮሚያ ክልል የበልግ ወቅት ዝናብ ላይ ጥገኛ  በመሆን የሰብል ምርት የሚያገኙ ናቸው ።  

በመጨረሻም   ሁሉም አርሶአደርና ባለድርሻ አካላት  በበልግ ወቅት የሚዘንበውን  ዝናብ በአግባቡ በመጠቀምና  የከርሰ ምድር ውሃ አቅምን ሥራ ላይ በማዋል  የተሻለ የበልግ የሰብል ምርትን ለማግኘት መረባረብ እንደሚገባ አቶ አለማየሁ ጥሪ አቅርበዋል ።

ኢትዮጵያ  በዘንድሮ የበልግ ወቅት ለእርሻ ሥራ  ከሚውለው ከ2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ  መሬት  በአጠቃለይ 3 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት ለመሰብሰብ  አቅዳለች ።