የቡና ጥራት መጓደል የኢትዮጵያ ቡና ወጪ ንግድ ላይ ከቡና ላኪዎች ጋር ጤናማ የሆነ ፉክክር ለማድረግ ተጽዕኖ እየፈጠረባቸው መሆኑን ቡና ቆይዎችና ላኪዎችና ባለድርሻ አካላት ገለጹ፡፡
በ15ኛው የአፍሪካ የቡና ጉባኤና ኢግዚቢሽን ላይ የተሳተፉ ቡና ቆይዎችና ላኪዎችና ባለድርሻ አካላት ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፣ ወደ ውጪ የሚላከውን የቡና ምርት በማሳደግ፣ የቡና ላኪዎችና ሌሎች የቡና ምርት ባለድርሻ አካላት ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል መንግሥት ድጋፉን ይበልጥ ሊያጠናክር ይገባል፡፡
ከአገሪቱ ወደ ውጭ የሚላከው ቡና ጥራት መጓደል በቡና ወጪ ንግድ ላይ ከሀገር ውስጥ ቡና ላኪዎች ጋር ጤናማ የሆነ ፉክክር ለማድረግ ተጽዕኖ እየፈጠረባቸው መሆኑን የሙለጌ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ መሐቡብ ሙስጠፋ አመልክተዋል፡፡
ሙለጌ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በ2008 በጀት ዓመት 8ሺህ 310 ቶን ጥራቱን የጠበቀ ቡና ወደ ዉጪ በመላክና የ39 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት በመቻሉ ከመንግስት የአንደኛ ደረጃ ላኪዎች ሽልማትን ተቀብሏል ፡፡
በተመሳይ ሁኔታ የአስቴር ቡና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ አስቴር መንገሻ በበኩላቸው በግብርና ምርቶች ማከማቻ መጋዘን እጦትና ከገዙት በደረጃ በታች የሆነ ቡና እየቀረበላቸው በመሆኑ ይበልጥ ውጤታማ እንዳይሆኑ እንቅፋት እንደሆነባቸው አመልክተዋል ፡፡
በአለም ገበያ የቡና ገበያ ዋጋ መውረድና መውጣትም በዘርፉ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው የገለጹት ደግሞ የለገሰ ሸሪፋ ቡና ላኪዎች ሥራ አስኪያጅ አቶ አሕመድ ለገሠ ናቸው፡፡
የተራራ ቡና የውጭ ንግድ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳምሶን ጌታቸው በበኩላቸው የተቆላ ቡና ወደ ውጭ ለመላክ የሚገዙት ቡና ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚቀርብና ደረጃውን ያልጠበቀ በመሆኑ ጥራት ላይ ችግር እየገጠማቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ተቆልቶ የሚሸጠው ቡና እሴት ሲጨመርበት ከጥሬ ቡና ከእጥፍ ዋጋ በላይ እንደሚሸጥና ይህ ተግባር ተጠናክሮ ቢቀጥል ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን አቶ ሳምሶን ጠቁመዋል፡፡
በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵያ የቡናና ሻይ ግብይት ባለስልጣን ድንገተኛ የጥራት ፍተሻ በማድረግ ችግሮቹን ለመቅረፍ ማቀዱን ነው ያስታወቀው፡፡
ለውጪ ገበያ የቀረበ ቡና ደረጃ ሲወጣለትና ሲመረመር ቡና አቅራቢው፣ የመጋዘን ድርጅት እና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ባለሙያዎች በተገኙበት እንዲሆንም መወሰኑን ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከቡና ምርት ጋር ሕይወታቸው የተቆራኘ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ፤ የቡና ኢንዱስትሪው ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነው ይሸፍናል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የቡና አምራች አገር ስትሆን ከ7 እስከ 10 በመቶ ለዓለም ገበያ በመላክ ከዓለም በ5ኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ አድርጓታል፡፡
ባለፈው ዓመት ለውጪ ገበያ ከቀረበው 183 ሺህ ቶን ቡና 780 ሚሊየን ዶላር ገቢ እንደገተገኘ መገለጹ ይታወሳል፡፡
ከ2ሺህ በላይ የአፍሪካ ልዑካን፣ ዓለም አቀፍ የቡና አዘጋጆች፣ ላኪዎች፣ አምራቾችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት 15ኛው የአፍሪካ ፋይን ኮፊ ጉባኤና ኢግዚቢሽን ከትላንት በስቲያ ተጠናቋል፡፡