በተለያዩ በልግ አብቃይ ክልሎች 2 ሚሊየን ሄክታር በሰብል መሸፈኑን የእርሻ እና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሚኒስትር ገለጸ ፡፡
የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማዮህ ብርሃኑ ለዋልታ እንዳስታወቁት፤በደቡብ ፣በኦሮሚያ ፣በአማራና በትግራይ ክልሎች በልግ አብቃይ በሆኑ አከባቢዎች ላይ ከ2 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ታርሶ በገብስ፣ጥራጥሬና በሌሎችም ሰብሎች ተሸፍኗል ፡፡
ከነዚሁም ውስጥ የደቡብ ክልል የበልግ አብቃይ አከባቢዎች ብቻ የሀገሪቱን እስከ 60 በመቶ እንደሚሸፍን ገልጸዋል ፡፡
ባለፈው ዓመት በነዚህ አከባቢዎች ላይ በነበረው የአየር ለውጥ መዛባት ሳቢያ የሚፈለገው ምርት ሊገኝ እንዳልቻለ ጠቅሰው፤ አሁን ግን የበልግ ዝናቡ ለአከባቢው አርሶ አደር ትልቅ እፎይታን የሚያጎናጽፍ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡
በበልግ አብቃይ ክልሎቹ ከተሸፈነው ሰብል 93 ሚሊየን ሄክታር ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ዓለማዮህ ገልጸዋል ፡፡
ይህም የመስኖ ምርት ሳይጨምር አሁን ከተመረተው ሰብል ተዳምሮ የሀገሪቱን የሰብል ምርት መጠን ወደ 400 ሚሊየን ኩንታል በላይ ከፍ እንደሚያደርገው ይታመናል ፡፡