የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን የሚገኘው ባዕኸር የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ መሰረተ ድንጋይ አስቀመጡ ፡፡
በመሰረተ ድንጋይ ማስቀመጥ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደገለጹት፤ የአርሶ አደሮችን ህይወት ለመለወጥ ዓላማው አድርጎ ይገነባል ፡፡
ፓርኩ ከወልቃይት ስኳር ፋብሪካ እና ከተከዜ ወንዝ ግድብ ጋር ተሳስሮ የሚገነባ መሆኑን ጠቅላይ መኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
በቓፍታ ሑመራ ወረዳ የሚገነባው ፓርክ በ4 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር የሚገነባና በ1ሺህ ሄክታር መሬት የሚያርፍ መሆኑን የክልሉ የኢንዳስትሪ ፓርኮች ልማት አስታውቋል ፡፡ ከዚሁም ውስጥ በ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ በ258 ሄክታር መሬት ለመጀመር በቅርቡ በሀገሪቱና በክልሉ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች መሰረተ ድንጋይ እንደሚያስቀምጡ ጠቁሟል ፡፡
በፓርኩ ወተትና ወተት ተዋጽኦ፣ ማርና ሰም፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ስጋ፣ ሰሊጥና ጨምሮ ከ40 በላይ የእርሻ ውጤቶች ለማቀናጀት መታቀዱን ነው የገለጸው ፡፡
ፓርኩ ስራውን ሲጀምር በማይ ካድራ፣ በሰቲት ሑመራ ፣ በዓዲጐሹ ፣ በዓዲ ሕርዲ ፣ በማይ ጋባ ፣ በዳንሻና በሽረ-እንዳስላሰ ከተሞች ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ የላቀ ለውጥ እንደሚያመጣ አመልክቷል ፡፡
የኢንዳስትሪው መጀመሪያው ምዕራፍ ሲጠናቀቅ ለ323 ሰዎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ፓርኩ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ደግሞ በቅጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለ3ነጥብ 2 ሚሊየን ሰዎች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጿል ፡፡
በትግራይ ክልል ከሚገነባው ባዕኸር የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ በተጨማሪ ሶስት ሌሎች ፓርኮች በደቡብ፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች ይገነባሉ፡፡
የአራቱም ፓርኮች ግንባታ በአራት ዓመት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ነው የተባለው ፡፡
ከአራቱ ፓርኮች ግንባታ በኋላ ደግሞ ተጨማሪ 13 የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ይገነባሉ ተብሎ ይጠበቃል ፡፡
በዚሁ የመሰረተ ድንጋይ ማስቀመጥ ስነ ስርዓት ላይ የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናትና የአከባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል ፡፡