ኢትዮጵያና ጣሊያን በጤናው ዘርፍ የአምስት ሚሊዮን ዩሮ ብድር ተፈራረሙ

ኢትዮጵያና ጣሊያን የጤና መሰረተ ልማቶችን ለማጠናከር የሚረዳ የአምስት ሚሊዮን ዩሮ የብድር ስምምነት ተፈራረሙ።

የብድር ስምምነቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፣በአማራና በደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች  የጤና መሰረተ ልማቶችን ለማጠናከር የሚውል መሆኑ ኢምባሲው ለዋልታ በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡

ለፕሮጀክቱ የሚስፈልገው ገንዘብ በጣሊያን የልማት ትብብር ኤጄንሲ በኩል የተለቀቀ ሲሆን፤ በ24 ወራት የሚከፈልና  አነስተኛ ወለድ የሚታሰብበት እንደሆነም ነው የተገለፀው፡፡

ስምምነቱን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እና በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ጁሴፔ ሚስትሬታ ፈርመዋል።

ስምምነቱ ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው አካባቢዎች ከጤና መሰረተ ልማት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታትና የጤና ዘርፉን ለማጠናከር እንደሚረዳ አቶ አድማሱ ገልጸዋል፡፡

ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለመስጠትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እንደሚረዳም ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል፡፡

የጣሊያን መንግስት በጤናው ዘርፍ ለሚከናወኑ ተግባራት የሚያደርገው ድጋፍ አገሪቱ በዘርፉ ለማከናወን ያቀደቻቸውን ተግባራት ለማሳካት ትልቅ አቅም እንደሚሆን አቶ አድማሱ አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ጁሴፔ ሚስትሬታ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ለምታከናውናቸው ልማቶች ኢጣልያ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በተለይም የጤና አገልግሎትን ለማሻሻልና ለማስፋፋት ኢጣልያ ከኢትዮጵያ ጋር በአጋርነት እንደምትሰራ ነው ያስረዱት፡፡

የብድር ስምምነቱ በተመረጡ 61 የጤና ማዕከላት ዘላቂ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እንዲኖር፣ የውሃ መሰረተ ልማት እንዲዘረጋ በማድረግ የሞትና የጉዳት መጠንን ለመቀነስ  እንደሚረዳ አምባሳደሩ አስገንዝበዋል፡፡

በአዲስ አበባ  የጣሊያን የልማት ትብብር ኤጄንሲ ኃላፊ  ጂኔቭራ ሌቲዚያ በብሔራዊ ደረጃ የተነደፈው የጤና ዕቅድን መሰረት ያደረገ መሆኑን አስታውሰው በተለይም የጤና  መሰረተ ልማት እጥረት ያሉባቸውን አካባቢዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ መከላከልን መሰረት ላደረገው የኢትዮጵያ የጤና ፖሊሲን ለማጠናከርም ድርሻው የጎላ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡