በቦሌ አራብሳ፣ በኮየፈጨና በቂሊንጦ ሳይቶች የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ነገ ይመረቃሉ

በ10/90፣ 20/80 እና 40/60 ፕሮግራሞች የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ነገ እንደሚመረቁ ተገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተመለከተው የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ በ40/60 የገነባቸውን 1 ሺህ 292 ቤቶችና የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኤጀንሲ በ10/90 እና 20/80 ፕሮግራሞች  የስገነቧቸው 39 ሺህ 220 ቤቶች ይመረቃሉ፡፡

 

በ11ኛው ዙር የወጡ የ20/80 እና በ10/90 39 ሺህ 220 ቤቶች የተወሰኑት ለልማት ተነሺዎች እንደሚሰጡም ነው የተናገሩት፡፡

ከንቲባው አክለው እንደገለፁት በተለይ በሰንጋ ተራ እና ክራውን ሆቴል አካባቢ የተገነቡት የ40/60 ቤቶች የመሰረት ልማት ሙሉ በሙሉ የተሟላላቸው ናቸው፡፡

በቦሌ አራብሳ፣ በኮየፈጨና በቂሊንጦ ሳይቶች የሚገኙትም የትምህርት ቤት፣ የጤና ጣቢያ የቴክኒክና ሙያን ጨምሮ ሌሎች ማሕበራዊ አገልግሎቶች እንደሚኖራቸው በጋዜጣዊ መግለጫው ተመልክቷል፡፡

የልማት ተነሺዎች የማሕበራዊ ግንኙነት እንዳይቋረጥ ለማድረግም ቀድሞ አንድ አካባቢ የነበሩ ነዋሪዎች በጋራ እንዲኖሩ እንደሚደረግም ተጠቅሷል፡፡

ከምረቃ በኋላም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ርክክብ በማድረግና የዕጣ ማውጣትና የ40/60 ቤቶች ቁጠባ አስቀድመው ሙሉ ለሙሉ ከፍለው ላጠናቀቁ ነዋሪዎችን ማስተላለፍ ቅድሚያ እንደሚሰጠው አቶ ድሪባ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ በመጀመሪያው ዙር የ40/60 ቤቶች ዕጣ ያልተካተቱ ነዋሪዎች በቀጣይ በሚወጡ ዕጣዎች ውስጥ እንደሚካተቱም ተገልጿል፡፡

ለቤቶቹ ግንባታ መንግስት 17 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የቀጥታ ድጎማ ማድረጉን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡