ሀብት ያፈሩ ከ500 በላይ አርሶ እና ከፊል አርብቶ አደሮች ተሸለሙ

 

በግብርና ዘርፍ ተሰማርተው ሃብት በማፍራት ወደ ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩ ከ550 በላይ አርሶ እና ከፊል አርብቶ አደሮች ተሸልመዋል ።

ሽልማት ከተበረከተላቸው አርሶ እና ከፊል አርብቶ አደሮች መካከል 60ዎቹ ሴቶች ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ በአዳማ በተከበረው ስምንተኛው ሀገር አቀፍ የአርሶ እና ከፊል አርብቶ አደሮች በዓል ተገኝተው ለሞዴል አርሶ እና ከፊል አርብቶ አደሮች ሸልማት ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር በሀገሪቱ ካሉ አርሶ አደሮች ውስጥ 22 በመቶ ሞዴል መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

እነዚህም በአከባቢያቸው ለሚገኙ አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች በማስተማር የሞዴሎች ቁጥር በሁለትና በሶስት እጥፍ ከፍ ለማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ  መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ፡፡

ሽልማት የተበረከተላቸው አርሶ እና ከፊል አርብቶ አደሮች በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ማስመዝገብ የቻሉ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በግብርናው ዘርፍ የሞዴል አርሶአደሮች ቁጥር እያደገ መምጣቱ ነው የተነገረው።

ተሸላሚዎቹ ሜዳሊያን ጨምሮ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሶስት ሺ ብር ቦንድና ዘመናዊ ትራክተር ተሸልመዋል።

ስምንተኛው የአርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች በዓል “በገጠር የስራ እድል በመፍጠር የግብርና ዘርፍ ቴክኖሎጂዎች የስርጸት ማእከል እንዲሆኑ በማድረግ የወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንረባረብ” በሚል መሪ ሀሳብ  በአዳማ ከተማ ተከብሯል፡፡

በአገሪቷ የገጠሩ ክፍል በግብርናው ዘርፍ ለሴቶችና ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል-(ኢዜአ)።