“መንግስት የህብረተሰቡ የመኖሪያቤት አንገብጋቢ ጥያቄ የመመለስ ጥረቱ አጠናክሮ ይቀጥላል” -ጠቅላይ ሚኒስትር

“መንግስት የህብረተሰቡ የመኖሪያቤት አንገብጋቢ ጥያቄ የመመለስ ጥረቱ አጠናክሮ ይቀጥላል” ሲሉ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ገለጹ ፡፡

“የህብረተሰቡ የመኖሪያቤት አንገብጋቢ ጥያቄ ለመመለስ መንግስት በአፍሪካ ደረጃ ግዙፍና የተቀናጀ የቤት ልማት ፕሮግራም ቀርጾ በመስራቱ በርካቶች ተጠቃሚ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ገልጸዋል ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቦሌ አራብሳና በቦሌ አያት ሳይቶች ግንባታቸው የተጠናቀቁ የ20/80 የቤት ፕሮግራሞችን በስፍራው ተገኝተው ሲመርቁ ፤ከሰው ልጆች መሰረታዊ ፍላጎቶች አንዱ የሆነውን የመጠለያ ጥያቄ መመለስ ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በሳይቶቹ የተመረቁ ቤቶች ለልማት ተነሺዎች የተላለፉ የቦሌ አያት ሶስት፣ አራትና አምስት 1ሺህ 811 እንዲሁም በቦሌ አራብሳ ሳይት 20 ሺህ 100 ቤቶች ናቸው።

በፕሮግራሙ በአዲስ አበባ ብቻ 175 ሺህ ቤቶች ለለግማሽ ሚሊዮን ዕድለኞች በዕጣ መተላለፋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን የተመረቁት ከ40 ሺህ በላይ ቤቶች ደግሞ የጥረቱን ውጤት የሚያሳዩ መሆናቸውን አስረድተዋል ።

መንግስት ከ40/60፣ 20/80 እና 10/90 ፕሮግራሞች በተጨማሪ የመንግስት ሰራተኞችና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በኪራይ መልክ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ፕሮግራም በመቅረጽም ወደ ስራ መግባቱ አመልክቷል ።

የሚያጋጥሙትን የክህሎትም ሆነ የገንዘብ ችግር በማሸነፍ የዜጎችን የቤት ጥያቄ ለመመለስ የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም አረጋግጠዋል።

በየከተሞቹ ያለውን የቤት ፍላጎት መንግስት ብቻውን ማሟላት ስለማይችል ዜጎች በተደራጀ መልኩ እንዲያግዙም ጠይቀዋል።

የአገር ውስጥ ባለሃብቶች እንዲሳተፉ በማድረግና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲሰማራ በማድረግ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ፍላጎት ለማሟላት ጥረት እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ የተሻለ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላትም እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ።

መንግስት ለህብረተሰቡ የሚያቀርባቸው ቤቶች የአገልግሎት ዘመናቸው እንዲረዝም ቤቶችን በመንከባከብና አካባቢውን ጽዱና አረንጓዴ በማድረግ ለመኖሪያ ምቹ አካባቢ መፍጠር ከነዋሪዎች ይጠበቃል ነው ያሉት ።

በከተሞች የሚንጸባረቁ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች መነሻ የሆነው ድህነትን ለመግታት ያልተቋረጠ ስራ እየተሰራ መሆኑ አስረድተዋል ።

በአዲስ አበባ ከተመረቁት ቤቶች በተጨማሪ 130 ሺህ ቤቶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ናቸው።

ከሚገነቡት መካከል የተወሰኑ ቤቶች በሚቀጥለው ዓመት ግንባታቸው እንደሚጠናቀቅም አስታውቀዋል።

በእስካሁኑ ሂደት የቤቶች ግንባታ የዜጎችን የቤት ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ፣ በስራ ዕድል ፈጠራ የከተማውን የተጎሳቆለ ገጽታ በመቀየር ጉልህ አስተዋጽዖ ማበርከቱን አንስተዋል-(ኢዜአ) ።