በአዲስ አበባ ከተማ በአሁኑ ወቅት 150 ሺ ወጣቶች ሥራ አጥ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ ።
በቢሮው የሥራ ዕድል ፈጠራ መርሃ ግብር አስተባባሪ አቶ ካሳ ስዩም ለዋሚኮ እንደገለጹት ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው የልየታና የማጥራት ሥራ በአጠቃላይ 150ሺ የሚሆኑ ዜጎች ሥራ አጥ ሆነው ተገኝተዋል ።
ቢሮው ባለፈው የበጀት ዓመት በሥራ አጥነት ከመዘገባቸው ወጣቶች መካከል 67ሺ የሚሆኑ አሁንም ሥራ ያላገኙ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ካሳ በዘንድሮ የበጀት ዓመት በተካሄደው ምዝገባ 83ሺ የሚሆኑ ሥራ አጦች ተመዝግበዋል ብለዋል ።
በዘንድሮ የበጀት ዓመት የወጣቶችን የሥራ ዕድል ፈጠራ መርሃ ግብርን ለማሳካት የቤት ለቤት ቅስቀሳ ጭምር በማድረግ ሥራ አጥ ወጣቶች በአንድ ማዕከል ተመዝግበው ካርድ እንዲወስዱ ተደርጓል ብለዋል አቶ ካሳ ።
በአዲስ አበባ ከተማ በ116 ወረዳዎች የሚገኙ አጠቃላይ ሥራ አጥ ወጣቶችን በመለየትና በማጥራት ረገድ የወጣቶች፣ የሴቶች አደረጃጃቶችና የህዝብ ክንፍ አባላት የተሳተፉ መሆኑን የገለጹት አቶ ካሳ ወጣቶች ሥራ አጥ መሆናቸውን በማጣራት የበኩላቸውን ሚና ተጫውተዋል።
ከምዝገባው ጎን ለጎን የወጣቶች የሥራ ዕድልን ፈጠራን ለማካሄድ የማመቻቸት ሥራ ተካሄዷል ያሉት ሥራ አጥ ወጣቶች በተለያዩ የሥራ መስኮች ለማሠማራት ለሁሉም የዘረፍ መሥሪያ ቤቶች ዕቅድ መሠጠቱን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።