የህዳሴ ግድብ ዋንጫ በደቡብ ክልል ከ320 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በተዘዋወረባቸው አካባቢዎች ከ320 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡ ተገለፀ፡፡

ዋንጫው በሃዲያ ዞን የሃያ ስድስት ቀናት ቆይታውን አጠናቆ ትናንት ወደ ወላይታ ዞን ሲገባ  ደማቅ አቀባበል እንደተደረገለት የክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ ጌታቸዉ አመልክተዋል፡፡

"የግድቡ ግንባታ የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን በማጠናከር ሃገራዊ መግባባትን የፈጠረ ነው "ብለዋል፡፡

ዋንጫው በሃድያ ዞን በነበረዉ ቆይታው ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ እንደነበረውም ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ለመሰብሰብ ከታቀደዉ 35 ሚሊዮን ብር የተለያዩ ስጦታዎችን ሳይጨምር ከ115 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

"ስራው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ለማሳተፍ በተካሄደ ንቅናቄ የተመራ በመሆኑ ከእቅድ በላይ ለመሰብሰብ ተችሏል " ያሉት ዳይሬክተሩ ህብረተሰቡ የቁጠባ ባህሉን በማሳደግ በሃገር ኢኮኖሚ ላይ የራሱን አስተዋጥኦ እንዲያበረክት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ጠቁመዋል፡፡

ዋንጫው በክልሉ በተዘዋወረባቸው ሶስት ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ በዓይነት የተበረከተው ስጦታ ሳይጨምር ከ320 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡንም ገልጸዋል፡፡

በወላይታ ዞን ዋንጫውን ለመቀበል ከፍተኛ ዝግጅት እንደተደረገና የህዝቡን ንቅናቄ በማስቀጠል የዞኑን እቅድ ለማሳካት ጥረት እየተደረገ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

ዋንጫው በሰባት ወረዳዎች ቆይታውን አጠናቆ መጋቢት 24 በዞኑ ዋና ከተማ ሶዶ እንደሚገባ የተዘጋጀዉ መርሃ ግብር ያሳያል፡፡

በዞኑ ለመሰብሰብ የታቀደውም ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

መጋቢት 24/ 2009ዓ.ም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ መሰረት ድንጋይ የቀመጠበት ስድስተኛ ዓመት በክልል ደረጃ የሚከበር ሲሆን በዞን ደረጃ ለዋንጫው የተሰበሰበው ገቢም ይፋ ይደረጋል ተብሏል፡፡