ማህበሩ ለካፒታል እቃዎች የሚውል 500 ሚሊዮን ብር መድቦ እየተንቀሳቀሰ ነው

በተለያዩ  የሥራ መስኮች ለሚሠማሩ ዜጎች ለካፒታል እቃ ግዥ የሚውል ገንዘብ መድቦ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የአዲስ ካፒታል እቃ ፋይናንስ  ንግድ ሥራዎች አክሲዮን ማህበር አስታወቀ ።

በማህበሩ  የፕላን ፣ ገበያና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መኩሪያ ለዋልታ እንደገለጹት ማህበሩ በዘንድሮ የበጀት ዓመት በተለያዩ የሥራ መስኮች ለሚሠማሩ 1ሺህ 500  ኢንተርፕራይዞች የሚውል  500 ሚሊዮን ብር መድቦ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ።

በተለይ በማኑፋክቸሪንና ኮንስትራክሽን ዘርፎች በመደራጀት በኢንተርፕራይዝ ደረጃ ለተቋቋሙ ማህበሩ ለሁለት ዓመት ያህል የካፒታል እቃዎችን ሲያቀርብ መቆየቱን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው ዘንድሮ በከተማ ግብርና በአገልገሎት ዘርፍ ለተሠማሩ ኢንተርፕራይዞች የካፒታል እቃ በማቅረብ ላይ ነው ።

በጥቃቅንና አነስተኛ የሚሠማሩ ዜጎች የካፒታል እቃ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ  ማህበሩ ከመደበው በጀት  በተጨማሪ  455 ሚሊዮን ብር ብድር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መጠየቁንም አቶ ጌታቸው አያይዘው ገልጸዋል ።

በአዲስ አበባ በተለያዩ የምርት ሥራ ለተሠማሩ ኢንተርፕራይዞች 1ሚሊዮን ብር የማይበልጥ የካፒታል እቃን በካፒታል ሊዝ አሠራር መሠረት ከማህበሩ  የሚያገኙ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጌታቸው ከ1 ሚሊዮን በላይ ዋጋ የሚያወጡ እዋዎችና ማሽነሪዎችን በኢትዮጵያ ልማት አማካኝነት እንደሚሠጥ ተናግረዋል ።

ማህበሩ የካፒታል እቃዎችንና ማሽነሪዎችን ከጉምሩክና ቀረጥ ነጻ በሆነ መልኩ ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባ ሲሆን  በሊዝ መሠረት የካፒታል እቃዎችን 15  በመቶ ወጪው  በመሸፈን ቀሪው ወጪ ክፍያ በ4 ዓመት በማጠናቀቅ የትላልቅ እቃዎችና ማሽናሪዎችን ባለቤት የሚሆኑበት መንገድ ነው ።

ማህበሩ እስካሁን  በሊዝ ፋይናንስ አሠራር መሠረት  47ነጥብ 3 ሚሊዮን  ብር የሚያወጡ የካፒታል እቃዎችን  በመግዛት 1ሺ 111 ለሚሆኑ ኢንተርፕራይዞች ማቅረቡን አቶ ጌታቸው አመልክተዋል ።

የአዲስ ካፒታል እቃ ፋይናንስ  ንግድ ሥራዎች አክሲዮን ማህበር በመጋቢት 2006 ዓም በ 500  ሚሊዮን ብር   የተከፈ  ካፒታል  የተቋቋመ ድርጅት ነው ።