ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የጎረቤት ሀገራትን ያስተሳስራል – ኢንጂነር አዜብ 

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ ሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋኑንና ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖረውን  የኃይል ትስስር እንደሚያጎለብተው ኢንጂነር አዜብ አስናቀ አስታወቁ፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበት ስድስተኛ ዓመት በዓል “ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሀገራችን ህብረ ዜማ የህዳሴያችን ማማ” በሚል መሪ ቃል ዛሬ በቦታው ተከብሯል፡፡ 

በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክተሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ እንደተናገሩት የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ ሀገራዊ የኤሌክትሪክ ሽፋኑን አሁን ካለበት 56 ከመቶ ወደ 90 ከመቶ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የጎላ አስተዋኦ ይኖረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ጎረቤት ሀገራትን በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር የተያዘውን እቅድ እንደሚያሳካም ነው ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ያብራሩት፡፡

የፕሮጀክቱ ግንባታ  57 ከመቶ መድረሱን ያበሰሩት ኢንጂነር አዜብ የሃይል ማመንጫ ቤቶች፣ የአየር ማረፊያ፣ የውስጥ ለውስጥመንገዶችና መሰል ግንባታዎች እየተፋጠኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱን ለፍጻሜ ለማብቃት በሶስት ፈረቃ ለ24 ሰዓት በመረባረብ ላይ ካሉ 10 ሺህ 500 ሰራተኞች ውስጥ ከሶስት በመቶ ያነሱት  የውጭ ሀገር ሙያተኞች መሆናቸውንም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል፡፡

ለግንባታው ከህብረተሰቡ ለመሰብሰብ ከታቀደው 12 ቢሊዮን ብር ውስጥ 9.6 ቢሊየኑ መሰብሰቡም ይፋ ሆኗል ሲል ኢዚአ ዘግቧል ፡፡