የአፍሪካ ልማት ባንክ ለአህጉሪቱ ገቢና ወጪ ባንክ የ450 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ።
ከባንኩ የተገኘው ገንዘብ በሚቀጥሉት አራት አመታት በአፍሪካ የገቢና ወጪ ንግድ ባንክ አማካኝነት የአፍሪካን እርስ በርስ ንግድና ከሌሎች አህጉራት ጋር የሚኖራቸውን የንግድ እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ ያግዛል ተብሏል።
ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 300 ሚሊዮን ዶላሩ ለንግድ ስራ ፓኬጅ ድጋፍ የሚውል ሲሆን ቀሪው 150 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ብሔራዊ የፋይናንስ ተቋማት ኪሳራ የመቋቋም አቅም ማሳደጊያ እንደሚሆን ባንኩ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
መግለጫው የልማት ባንኩ እነዚህን ተግባራት እውን ለማድረግ አምስት ቅድሚያ ለሰጣቸው ለአፍሪካ እርስ በርስ ንግድ ትስስር፣ለሃይል ልማት፣ለምግብ ዋስትና፣ ለማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ልማትና ሌሎች ስራዎች ለማሰፈፀም ይውላል።
የአፍሪካ ገቢና ወጪ (ኤግዚም) ባንክ በአፍሪካውያን መካከል የሚደረገውን የእርስ በርስ ንግድ ልውውጥና አህጉሪቷ ከሌሎች ክፍለ ዓለማት ጋር ያላትን ንግድ ለማጎልበት የተቋቋመ የፋይናንስ ተቋም ነው-(ኢዜአ) ።