አርሶ አደሩ ለግድቡ ግንባታ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነዉ

ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የአርሶና አርብቶ አደሩ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉንና በተለይም በተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ከ49 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሥራ መሰራቱ ተገለፀ፡፡

የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትርና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግምባታ የህዝብ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በአርሶና አርብቶ አደሩ የነቃ ተሳትፎ በስፋት እየተከናወኑ የሚገኙት የአካባቢ ጥበቃና የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ሥራዎች የግድቡን ዕድሜ ለማራዘምና ግድቡን ከደለል ሙሌት ለመታደግ ድርሻቸው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

እስከ አሁን በአርሶና አርብቶ አደሩ የተከናወኑት የአካባቢ ጥበቃና የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ሥራዎች ከ49 ቢሊዮን ብር በላይ ሲገመቱ ባለፈው ዓመት ብቻ ከተከላቸው አራት ቢሊዮን ችግኞች ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት ፀድቀዋል፡፡

ዶክተር ደብረፅዮን አርሶ አደሩ በቦንድ የሚደርገውን ድጋፍ ለማጠናከር በቀጣይ የተደራጀና የተጠናከረ ሥራ እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡

እስከአሁን በነበረው ሂደት አርሶና አርብቶ አደሩ በራሱ ተነሳሽነት ቦንድ በመግዛት ከሚያደርገው ድጋፍ በስተቀር በተደራጀ መልኩ የማስተባበር ሥራው ብዙ አልተኬደበትም ነበር፡፡

አርሶና አርብቶ አደሩ በገንዘብና በጉልበት ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ በዓይነትም ድጋፍ ከማድረግ አልተቆጠበም፡፡ በቅርቡ በየካቲት ወር መጨረሻ በዱራሜ፣ስልጤና ጉራጌ ዞኖች ብቻ ከ300 በላይ ከብቶችን አበርክቷል፡፡

አርሶና አርብቶ አደሩ በአካባቢ ጥበቃና በተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ዘርፍ ዘላቂ ሥራዎችን በማከናወን ያልተቆጠበ ድጋፉን እያደረገ ይገኛል፡፡ የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመርን ተከትሎ በዓመት 30 ቀን የተፈጥሮ ሀብት ክብካቤ ሥራ ያከናውናል፡፡

ዋልታ በጉዳዩ ዙሪያ ካናገራቸዉ አርሶ አደሮች መካከል አንዱ የሆኑት አርሶ አደር ገለታ ደምሰው ባለፈው ዓመት የ30ሺ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ይናገራሉ፡፡ ግንባታው እስከሚጠናቀቅ ድረስም ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ ቆርጠው መነሳታቸውን አስገንዝበዋል፡፡

አርሶ አደር ኃይለ በርሀ እና አይናዲስ ሞላም በበኩላቸዉ በተለያዩ ጊዜያት ቦንድ በመግዛት ለህዳሴው ግድብ ድጋፋቸውን በተግባ ማረጋገጣቸውን ነው የገለፁት፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል የማመንጨት አቅም በተለያዩ ጊዜያት በተከናወኑት የማሻሻያ ሥራዎች ከ5250 ሜጋ ዋት ወደ 6450 ሜጋ ዋት አድጓል፡፡ ለአገር ውስጥ ሙያተኞች ከፍተኛ የቴክሎጂ ሽግግርን ከመፍጠር በተጓዳኝ እስከ አሁን ድረስ ለ11ሺ ያህል ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡